አሜሪካ በሶሪያ ንጹሃንን የገደለውን የአየር ጥቃቷን 'ትክክለኛ' ስትል ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መከላከያ በአውሮፓውያኑ 2019 ላይ ሶርያ ውስጥ ለንጹሃን ዜጎች ሞት መንስኤ የሆነውን የአየር ጥቃት ትክክለኛ እና ተገቢ ነበር ብሎታል።
በወቅቱ አሜሪካ ጥቃቱን ስታደርስ የኢስላሚክ ስቴት ተዋጊ የሆኑ 80 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ቡድኑም በቦታው የመጨረሻ ፍልሚያውን እያደረገ ነበር።
አሜሪካ የአየር ጥቃቱን ካደረሰች በኋላ ከሟቾቹ መካከል 16ቱ የአይሲሲስ ተዋጊዎች ናቸው ብላለች። አራቱ ደግሞ ንጹሀን ዜጎች መሆናቸውን አምናለች።
ነገር ግን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሞተዋል ከተባሉት ሰዎች ከ60 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ላይ የተገኘ ይፋዊ ማስረጃ የለም ያሉ ሲሆን፤ ምናልባትም ተጨማሪ ንጹሀን ዜጎች ሞተው ሊሆን እንደሚችል የጦሩ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ከሆነ የአሜሪካ መከላከያ ጥቃቱን ለመሸፋፈን የሞከረ ሲሆን፤ እስካሁን በተፈጸመው የአየር ጥቃት ላይም ቢሆን በገለልተኛ አካል ምርመራ አልተደረገም።
የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2019 ላይ ሲሆን፤ ቦታው ደግሞ በምሥራቃዊ ሶሪያ በምትገኝ ባጉዝ በተባለች ከተማ ውስጥ ነው። በወቅቱ ከተማዋ አይሲስ የያዛት የመጨረሻዋ ጠንካራ ቦታ ነበረች።
ምንም እንኳን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ቅኝት በሚያደርጉት ወቅት በርካታ ንጹሀን ዜጎች መኖራቸውን ቢያመለክቱም የአሜሪካ ተዋጊ ጀቶች ግን በፍጥነት ሦስት ቦምቦችን በርካታ ሰዎች ወደሚገኙበት ቦታ መልቀቃቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላም የጦር አዛዦች ስለደረሰው ሰብአዊ ጉዳት እና መደረግ ስላለበት ምርመራ የተነገራቸውን ችላ ከማለታቸው በተጨማሪ የአሜሪካ መከላከያ ዋና መርማሪ ስለ ጥቃቱ ምንም አይነት ነገር እንዳይነገሩ መከልከላቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። አክሎም እስካሁን ምንም አይነት ገለልተኛ ምርመራ አልተደረገም ብሏል።
"ከፍተኛ አመራሮች ይህ ጉዳይ ይፋ እንዲወጣ የፈለጉ አይመስሉም። እስካሁንም ምንም ለማድረግ ፈቃደኛ አይደሉም" ብሏል ጉዳዩን ሲከታተለው የነበረውና በዚሁ ምክንያት ከሥራው መባረሩን የሚገልጸው ጌን ታት።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ግን ውንጀላውን አልቀበለውም ብሏል።
የጦሩ ቃል አቀባይ ካፕቴን ቢል አርባን ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ፤ የአሜሪካ ወታደሮች በወቅቱ ጥቃቱን ሲፈጽሙ ምንም አይነት ንጹሀን ዜጎች ስለመኖራቸው መረጃው እንዳልነበራቸው ገልጸዋል።
ነገር ግን ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የአሜሪካ ወዳጅ የሆነ አገር ሰው አልባ አውሮፕላን ባቀረበው ምስል ላይ በአካባቢው ንጹሀን ዜጎች መኖራቸውን አመላክቷል ብለዋል።
ይህን ምስል መሠረት በማድረግም 16 የአይሲስ ተዋጊዎችና አራት ንጹሀን ዜጎች መሞታቸው መረጋገጡን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ነገር ግን በጥቃቱ ተጨማሪ ከ60 በላይ ሰዎች ስለመሞታቸው ተጨባጭ መረጃ የለንም ብለዋል።
"በወቅቱ እርግጠኛ መሆን ያልቻልንበት ምክንያት በርካታ ሴቶችና ቢያንስ አንድ ህጻንን ጨምሮ ሌሎችም መሳሪያ መያዛቸው በቪዲዮ በመታየቱ ሲሆን በወቅቱም በትክክል የታጠቀውንና ያልታጠቀውን መለየት አልቻለንም። በጥቃቱም የተገደሉት አብዛኛዎቹ የቡድኑ ታጣቂዎች ናቸው። ነገር ግን በወቅቱ በተደረጉት ሁለት የአየር ጥቃቶች ተጨማሪ ንጹሃን ዜጎች ነበሩ" ብለዋል።
አክለውም ከጥቃቱ በኋላ ምርምራ መደረጉንና ሁለቱም የአየር ጥቃቶች እራስን ለመከላከል የተወሰዱ ስለመሆናቸው መወሰኑን ገልጸዋል። ከምርመራው በኋላም ምንም አይነት የሥነ ምግባር እርምጃ አልተወሰደም ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ኒው ዮርክ ታይምስ ጥቃቱን በተለመከተ ኃላፊዎች ለመሸፋፈን እየሞከሩ ነው ብሎ ስለሰራው ዘገባ ግን ምንም አይነት አስተያየት አልሰጡም።












