ኤፍቢአይ ከራሱ ኮምፒውተር የተላኩ ሃሰተኛ ኢሜይሎችን እየመረመረ ነው

የኤፍቢአይ ህንፃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የሳይበር ጥቃት ሊኖር እንደሚችል በማስጠንቀቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሃሰተኛ ኢሜይሎች በኤፍቢአይ ከሚገኘው ቢሮ በአንደኛው ኮምፒውተር መላኩን ተከትሎ ቢሮው ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።

የፌደራል ምርመራ ማዕከል የሆነው ይህ የመንግሥት ኤጀንሲ በትናንትናው ዕለት ቅዳሜ የተከሰተው ሁኔታ ላይ በሂደት ላይ ያለ ምርመራ ከማለት ውጭ ምንም አይነት ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫ አልሰጠም።

የተላኩት ሃሰተኛ መልዕክቶች ከአሜሪካ የሃገር ውስጥ ደህንነት ክፍል እንደተላኩ ተደርገው ነው የወጡት።

መልዕክቶቹ ይደርሳል ስለተባለው ስጋት ማስጠንቀቂያ ሲሆን ለደረሳቸውም ግለሰቦች የተራቀቀ የሰንሰለት ጥቃት ኢላማ ሆናችኋል የሚልም ተካቶበታል።

ለትርፍ ያልተቋቋመውና የማይፈለጉ መልዕክቶችን በማጣራት የሚታወቀው ስፓምሃውስ የተባለው ድርጅት እንዳስታወቀው ጥቃቱ ዳርክ ኦቨርሎድ ተብሎ ከሚጠራው የዘረፋ ቡድን እንደሚመጣም መልዕክቱ ላይ ይገኝበታል ብሏል።

"በኢሜይሉ ላይ የተካተቱት የራስጌዎቹ አርማ እውነተኛ በመሆናቸውና ከኤፍቢአይ ኮምፒተርም በመላካቸው በበርካቶች ላይ ረብሻ እየፈጠሩ ነው" ሲል ስፓምሃውስ በትዊተር ገጹ ያስታወቀ ሲሆን ሆኖም እነዚህ ኢሜይሎች የላኪውን ስም ወይም አድራሻ አላካተቱም ብሏል።

የአሜሪካ ሚዲያዎች እንደዘገቡት በዚህ ወቅት ከ100 ሺህ በላይ ኢሜይሎች ተልከዋል።

ኤፍ ቢአይ በበኩሉ ቅዳሜ እለት በሰጠው መግለጫ የኤፍቢአይን ስም ያካተቱ ሃሰተኛ ኢሜይሎች ማግኘቱን አስታውቋል።

ችግሩ ከታወቀ በኋላ የተላከበት ኮምፒውተርና ሃርድዌር ከኢንተርኔት ግንኙነት ውጭ የተደረገ መሆኑን የገለጸው ኤጀንሲው ህብረተሰቡ "ከማይታወቁ ላኪዎች እንዲጠነቀቅ" እና አጠራጣሪ ድርጊቶችን ለመንግሥት እንዲያሳውቅ አስጠንቅቋል።

ኢሜይሎቹ የተላኩት የኤፍቢአይ ኮምፒውተሮችን ለመጠቀም ፍቃድ ካለው ግለሰብ ይሁን በመረጃ መንታፊዎች አማካኝነት እንደሆነ እስካሁን ግልፅ አይደለም።