በኢኳዶር እስር ቤት በተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል በተነሳ ግጭት 68 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢኳዶር መስከረም ወር ላይ ከመቶ በላይ ታራሚዎች በሞቱበት እስር ቤት በተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል አዲስ ግጭት ተቀስቅሶ 68 ታራሚዎች መሞታቸውን ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
በኢኳዶር የወደብ ከተማ ጉዋያኪል በሚገኘው የሊቶራል ማረሚያ ቤት አምባጓሮው አርብ ማምሻውን መነሳቱ ተዘግቧል።
ወደ ወህኒ ቤት ህንፃው የገቡት ፖሊሶች ሽጉጥ፣ ፈንጂ እና ስለት ማግኘታቸውን ዘገባዎች ጠቁመዋል።
በያዝነው የፈረንጆቹ አመት ብቻ በሀገሪቱ እስር ቤቶች 300 የሚጠጉ እስረኞች ሞተዋል።
በመስከረም የደረሰው የተቀናቃኝ ወሮበሎች ቡድን ግጭት በኢኳዶር ታሪክ እጅግ የከፋ ነበር።
በወቅቱም ከእስር ቤቱ አንደኛው ክንፍ ወደ ሌላ ክንፍ ለመሸጋገር ጉድጓድ ውስጥ ለውስጥ በመሄድ በተቀናቃኝ የቡድን አባላት ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
የማረሚያ ቤቱን ግቢ መልሶ ለመቆጣጠር በመቶዎች የሚቆጠሩ መኮንኖች እና የጦር ሰራዊት ወታደሮች ተሰማርተው ነበር።
በዚህ አሰቃቂ ጥቃት አንዳንድ ታራሚዎች አንገታቸው ተቆርጦ የታዩ ሲሆን በኢኳዶር ውስጥ ሜክሲኮ መሰረታቸውን ያደረጉ ሲናሎአ እና ጃሊስኮ ኒው ጄኔሬሽን ካርቴልስ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ የወንጀለኞች ተጽዕኖ እያደገ መምጣቱ ትኩረት ስቧል።
በያዝነው ሳምንት አርብ በደረሰው ግጭት ከሞቱት በተጨማሪ 25 ታራሚዎች የቆሰሉ ሲሆን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በትጥቅ ጭምር በታገዘ ግጭት ሶስት እስረኞች በጥይት ተገድለዋል።
ቅዳሜ እለትም በማረሚያ ቤቱ ተጨማሪ ብጥብጥ እንደነበረ የተዘገበ ሲሆን ተጨማሪ ወታደሮችም ተሰማርተው ከእስር ቤቱ ግቢ ውጭ በመኪኖች ሲጠብቁ ነበር ተብሏል።
የታራሚዎች ቤተሰቦች እና ወዳጆች ከእስር ቤቱ ህንፃ ውጭ ተሰብሰው መረጃ ለማግኘት ሲጠባባቁ የነበረ ሲሆን የተጎጂዎች ስም ዝርዝርም ውጭ እንዲለጠፍ ተደርጓል።
ባለስልጣናቱ እንደሚሉት አምባጓሮው የተነሳው አንደኛው የወሮበሎች የቡድን መሪ ቀደም ብሎ ከእስር ከተፈታ በኋላ ሲሆን ይህም በተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል በተፈጠረ የግዛት ውዝግብ ነው።












