አምስት ሰልፈኞች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸው የሱዳን ዶክተሮች ቡድን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሱዳን ውስጥ ትናንት ቅዳሜ ዕለት ዴሞክራሲን በመደገፍ ሰልፍ ሲያካሂዱ የነበሩ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የሱዳን ዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ።
ቡድኑ እንዳለው አራት ሰልፈኞች በተተኮሰባቸው ጥይት ሲሆን ሕይወታቸው ያለፈው አምስተኛው ግለሰብ ደግሞ በተተኮሰ አስለቃሽ ጭስ ታፍኖ ነው ሕይወቱ ያለፈው።
በመላው ሱዳን በሚገኙ ትልልቅና አነስተኛ ከተሞች የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት በመቃወም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአገሬው ዜጎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ፖሊስ እስካሁን ሰልፈኞቹን ለመበተን ጥይት አልተጠቀምኩም በማለት በተቻለ መጠን አነስተኛ ኃይል ለመጠቀም ሞክሬያለሁ ሲል አስታውቋል።
ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው የዜና ወኪልም ከተቃዋሚ ሰልፈኞቹ በተሰነዘረ ጥቃት ምክንያት 39 የፖሊስ አባላት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዘግቧል።
ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነው ተቃውሞ የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይቋቋም በሚል ለተቃውሞ ሰልፍ በወጡ ዜጎች እና ፖሊስ መሀል ግጭት በመፈጠሩ ነው።
ባሳለፍነው ሐሙስ ደግሞ በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት በመምራት ወታደሩ ሥልጣን እንዲይዝ ያደረጉት ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሐን አዲስ ምክር ቤት ሲመሠርቱ እራሳቸውን ደግሞ መሪ አድርገው ሰይመዋል።
ጄነራል ቡርሐን፤ ምክትላቸው መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችን ከጥቅምት 25ቱ መፈንቅለ መንግሥት በፊት በነበራቸው ሥልጣን እንዲቆዩ አድርገዋል።
ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሽግግር መንግስት በቶሎ እንዲቋቋም ሲጠይቅ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያንምም ይህንኑ ጥያቄ በመያዝ ነው አደባባይ የወጡት።
ቅዳሜ ዕለት የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በከፍተኛ የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ነው ተብሏል። እንደ ፓሪስ እና በርሊን ባሉ የአውሮፓ ከተሞችም ተመሳሳይ መልዕክት ያለው የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው በዋና ከተማዋ ካርቱም የነበሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ''ወታደራዊ አገዛዝ በቃን'' እና ''መላው ወታደራዊ ካውንስል ይውረድ'' የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር።
የሱዳን ዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልእክት በዚሁ ሰልፍ ላይ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን እና በርካታ ሰልፈⶉች ደግሞ ጉዳት ማስተናገዳቸውን አስታውቋል።
ቡድኑ አክሎም የጸጥታ ኃይሎች በእምዱርማን የሚገኘውን ሆስፒታል በድንገት በመውረር ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎችን ይዘው መሄዳቸውን ገልጿል።












