በኒጀር ትምህርት ቤት ውስጥ በተቀሰቀሰ እሳት ቢያንስ 25 ህጻናት ሞቱ

የኒጀር መማሪያ ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በደቡባዊ ኒጀር በሳር ጎጆ መማሪያ ክፍል ላይ በተነሳ እሳት ዕድሜያቸው ከአምስት እስከ ስድስት የሚሆኑ ቢያንስ 25 ህጻናት ለህልፈት መዳረጋቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

መነሻው ያልታውቀው እሳት ሰኞ ማለዳ ላይ በሀገሪቱ ማራዲ በተሰኘው ግዛት ውስጥ ህጻናት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ በርካታ ሰዎች ቆስለውበታል።

በኒጀር ትምህርት ቤቶች ውስጥ በመደበኛ ሁኔታ የተገነቡ ክፍሎች ተማሪዎች ማስተናገድ በማይችሉበት ጊዜ ተጨማሪ ክፍሎችን በእንጨት እና ጭድ መስራት የተለመደ ነው።

ታዲያ የሰኞው ቃጠሎ በዚህ ሁኔታ የተሰሩ ሶስት የመማሪያ ክፍሎችን ማውደሙን የማራዲ ከተማ ከንቲባ ቻይቡ አቡባካር ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

በርካታ አስከሬኖች ከስፍራው ሲነሳ እና በርካታ የተጎዱ ህጻናት ደግሞ ወደ ሆስፒታል ሊወሰዱ በተሽከርካሪ ሲጫን አይቻለሁ ሲሉ የአንድ የአይን እማኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በእሳት ቀጠሎ ከተጎዱት ውስጥ አስጊ ሁኔታ ላይ ያሉ መኖራቸው ተነግሯል።

በአደጋው ምክንያትም ትምህርት ቤቱ ትምህርት አቋርጣል።በኒጀር በትምህርት ቤት ክፍሎች ውስጥ የእሳት ቃጠሎ የተለመደ ቢሆንም በዚህ መጠን ሞት የመከሰት ሁኔታው ግን ጣባብ ነበር።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ በትምህርት ቤት በተቀሰቀሰ እሳት ማምለጥ ያልቻሉ 20 ህጻናት ህይወታቸው አለፏል።

በዚያ ክስተት በአጠቃላይ 28 ከሳር የተሰሩ ክፍሎች የወደሙ ሲሆን አደጋው ህዝባዊ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር።

በአደጋው ማምለጥ ሳይችሉ ለህልፈት የተዳረጉት አብዛኞቹ ህጻናት በመዋእለ ሕጻናት ውስጥ የነበሩ ናቸው።