አዲሱ የኒው ዮርክ ተመራጭ ከንቲባ ደመወዝ በቢትኮይን ይከፈለኝ አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ተመራጩ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ የመጀመርያ የሦስት ወር ደመወዜን መቀበል የምፈልገው በተለመደው የወረቀት የገንዘብ ኖት ሳይሆን በዲጂታል ገንዘብ ቢትኮይን ነው አሉ።
ቢትኮይን ኦንላይን የሚቀመጥ የማይዳሰስ ከከክሪፕቶከረንሲ የዲጂታል ገንዘብ ሥርዓት አንዱ ነው። ክሪፕቶከረንሲዎች እንደተለመደው የገንዘብ ኖቶች በብሔራዊ ባንኮች የሚታተሙ አይደሉም።
የቀድሞው የፖሊስ አዛዥና የአሁኑ የኒው ዮርክ ተመራጭ ከንቲባ በዚህ ሳምንት ነበር በከንቲባነት የተመረጡት።
ከንቲባነታቸውን ያላጠናቀቁትን ቢል ዴ ብላሲኦን ቦታ የሚረከቡትም በመጪው አዲሱ የፈረንጆች ዓመት ጥር ነው።
ሰዎች የዚህ ዲጂታል ገንዘብ ባለቤት የሚሆኑት ‹ማይኒንግ› በሚባል ሂደት ሲሆን፣ ቁጥጥር የሚደረግበትም በመላው ዓለም በተሳሳሩ ኮምፒውተሮች እንጂ በባንኮች አይደለም።
ከንቲባ አዳምስ በማኅበራዊ የትስስር መድረክ እንደተናገሩት ደመወዝ በቢትኮይን እንዲከፈላቸው የፈለጉት ኒው ዮርክን ወደፊት የክሪፕቶከረንሲ ኡንዱስትሪ መናኸሪያ ለማድረግ ያላቸውን ትልም ለማመላከት ነው።
የቢትኮይን ዋጋ በዓለም ላይ ፍጹም በማይገመት ሁኔታ ከፍና ዝቅ የሚል ሲሆን ይህ የዲጂታል ገበያ ሥርዓት የተፈጠረውም በፈረንጆቹ በ2009 ነበር።
ከክሪፕቶከረንሲዎች ቀድሞ የተወለደው ቢትኮይን የሚባለው ነው፤ በግዝፈቱም በሚያንቀሳቅሰው የገንዘብ ሥርዓትም የሚስተካከለው የለም።
ከተመራጭ ከንቲባ አዳምስ በፊትም በተመሳሳይ የማያሚ ከተማ ከንቲባ የመጀመርያ ወር ደመወዜን በቢትኮይን ክፈሉኝ ብለው ነበር።
የማያሚው ከንቲባ ፍራንሲስ ሱዋሬዝ በትዊተር ሰሌዳቸው ይፋ እንዳደረጉት በድጋሚ ከንቲባነት ሲመረጡ በቢትኮይን እንዲከፈለኝ እፈልጋለሁ ብለዋል።
ከንቲባ ሱዋሬዝም በተመሳሳይ ማያሚ ከተማን የክሪፕቶከረንሲ ዲጂታል የግብይት ሥርዓት መናኸሪያ እንድትሆን ይሻሉ።
አዳምስ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ነው ለኒውዮርክ ከንቲባነት የተመረጡት። የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል የሆኑት ሚስተር አዳምስ ለከተማዋ በታሪክ ሁለተኛው ጥቁር ከንቲባ ናቸው።












