የአሜሪካ ወታደራዊ መኮንኖች የሲአይኤን የማሰቃየት ተግባር ሃገሪቱን ያጠለሸ ሲሉ ወቀሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በወታደራዊ ዳኝነት ውስጥ የሚያገለግሉ ሰባት የአሜሪካ ከፍተኛ መኮንኖች ሲአይኤ በአንድ እስረኛ ላይ ፈጽሟል የተባለውን ማሰቃየት "የአሜሪካ ሞራል ያጠለሸ ነው" ሲሉ ወቀሱ።
በኒውዮርክ ታይምስ የታተመውና በዳኞቹ የተጻፈው የምህረት ደብዳቤ የማጂድ ካንን አያያዝ ያወግዛል።
ካን በአልቃይዳ ተላላኪነት መሥራቱን አምኖ በፓኪስታን ውስጥ ከተያዘበት እአአ በ2003 ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።
በአሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2011 በደረሰው፣ 9/11 ተብሎ በሚጠራው ጥቃት ወዲህ በባህር ማዶ በሚገኝ የሲአይኤ ጣቢያ ታስሮ በነበረ እስረኛ የተሰጠ የመጀመሪያው ምስክርነት ነው።
መደብደቡን፣ ተዘቅዝቆ ፊቱን ጨርቅ ሸፍኖ ውሃ በመፈቅ መሰቃየቱንና እና በጨለማ በሰንሰለት ታስሮ መቆየቱን ጨምሮ ተፈጸመብኝ ስላለው ጥቃት ባለፈው ሳምንት መስክሯል።
በሲአይኤ ጣቢያ "በተባበርኩ ቁጥር ብዙ እሰቃይ ነበር" ያለ ሲሆን መርማሪዎችን ለማስደሰት ሲል መዋሸት እንደጀመረም ተናግሯል።
ካን በፓኪስታን አድጎ በ16 ዓመቱ ነው ወደ አሜሪካ ያቀናው። ለድርጅቱ በተመለመለበት ወቅት "ታዳጊ፣ በብዙ ነገሮች የሚደነቅ እና ተጋላጭ ልጅ" እንደነበር ገልጿል።
አሁን 41 ዓመት የሞላው ካን አል-ቃይዳን እና ሽብርተኝነትን እንደማይቀበል ተናግሯል።
ጠበቃው ደንበኛቸው በቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ መረጃ ለአሜሪካ የስለላ ባለስልጣናት ቢያካፍልም በእስር ቤት ውስጥ "አስከፊ እና አሳፋሪ የማሰቃየት ተግባር" እንደተፈጸመበት ተናግሯል።
ካን ባለፈው ሳምንት በኩባ በሚገኘው የጓንታናሞ ቤይ የባህር ሃይል ጣቢያ ለተሰየመው ችሎት ባለ 39 ገጽ ቃሉን አንብቧል።
በሰጠው ምስክርነት እርቃኑን እንዲሆን፣ ፊቱ ተሸፍኖ በፊንጢጣው በኩል ፈሳሽ እንዲገባ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዋራጅ ተግባራት እንደተፈጸሙበት ዘርዝሯል። የእንቅልፍ እጦት፣ በግዳጅ መመገብ እና በመርማሪዎች በሰንሰለት ተሰቅሎ እንዲታሰር መደረጉንም ገልጿል።
ደረሰብኝ ያለው አብዛኛው ጉዳይ እአአ በ2014 የወጣውንና የሲአይኤ የምርመራ ፕሮግራም ያጠናቸውን ቁልፍ የሪፖርት ግኝቶችን ያንጸባርቃል።
ካን የ2002 የአልቃይዳ ሴራዎችን መረዳቱን ካመነ በኋላ የ26 አመት እስራት ባለፈው ሳምንት ተፈርዶበታል። የቅጣት ዝቅተኛውን የአወሳሰን መመሪያ የተከተለ ነው ።
ከስምንቱ ወታደራዊ ዳኞች መካከል ሰባቱ ምሕረት እንዲደረግለት በጻፉት ደብዳቤያቸው የካንን አያያዝ "ከስለላ አንጻር ምንም ዓይነት ተግባራዊ ፋይዳ የሌለው ወይም ለአሜሪካ ሌላ ተጨባጭ ጥቅም የለውም" ብለዋል።
"ይልቁንስ በአሜሪካ የሞራል ልዕልናን ያጠለሸ ነው። ካን በአሜሪካ ወታደሮች እጅ ያለው አያያዝ ለአሜሪካ መንግስት አሳፋሪ ሊሆን ይገባል" ሲል ደብዳቤው አክሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ ሪፖርቶች እንደሚናገሩት የ41 አመቱ ግለሰብ እአአ በ2012 ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በኋላ ከባለስልጣናት ጋር በነበረው ትብብር ላይ በተመሠረተ የይግባኝ ስምምነት ለሁለት አስርት ዓመታት በአሜሪካን እስር ቤት ከቆየ በኋላ በመጪው የካቲት ድረስ ሊለቀቅ ይችላል።












