ኬንያ ያልተከተቡ ሰዎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ልታግድ ነው

ታትሟል

ኬንያውያን የኮቪድ-19 ክትባት ካልወሰዱ ከታኅሣሥ 21 ጀምሮ የሕዝብ ማመላለሻን ጨምሮ የመንግሥት አገልግሎቶችን አያገኙም ሲሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ሙታሂ ካግዌ ተናግሩ።

እገዳው አውቶቡሶችን፣ ታክሲዎችን፣ ባቡሮችን እና የአገር ውስጥ በረራዎችን እንደሚያጠቃልል ገልጸዋል።

በተጨማሪም እገዳው የሆስፒታል እና የእስር ቤት ጉብኝትን ጨምሮ በትምህርት፣ በኢሚግሬሽን እና በግብር ቢሮዎች ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል።

እስካሁን ከአገሪቱ ሕዝብ ከ10 ከመቶ ያነሱ ኬንያውያን ብቻ ናቸው የወረርሽኙን መከላከያ የተከተቡት።

ኦፊሴላዊው መረጃ እንደሚያሳየው ኬንያ ከተቀበለችው 10.7 ሚሊዮን ክትባት ውስጥ 6.4 ሚሊዮኑን ብቻ ነው የከተበችው።

ሆኖም በአገሪቱ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊነት ዝቅተኛ ነው። ሮይተርስ የዜና ወኪል ባጠናቀረው መረጃ መሠረት በየቀኑ በአማካይ 59 አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ።

የካግዌ መግለጫ በቅርቡ ከሚከበሩት የአዲስ ዓመት እና የገና በዓላት በፊት የክትባት ዘመቻውን ለማጠናከር ያለመ ይመስላል። በበዓላት ሰሞን ጉዞ እና ማኅበራዊ ግንኙነት ስለሚጨምር ሰዎች በበሽታው የመጠቃት ዕድላቸው ይጨምራል።

መንግሥት በታኅሣሥ ወር መጨረሻ ለ10 ሚሊዮን ሰዎች ክትባት ለመስጠት አቅዷል።

ይህም ከጠቅላላው ሕዝብ 20 በመቶውን ብቻ ስለሚይዝ አብዛኛው ሕዝብ የመንግሥት አገልግሎቶች ላያገኝ ይችላል።

እገዳዎቹ ሁሌም በጥብቅ ተፈጻሚ ላይሆኑ ይችላሉም ሲሉ ካግዌ ጠቅሰዋል።

ካግዌ "ኬንያውያን እስከ ታኅሣሥ 21 ድረስ ክትባቱን እንዲወስዱ ጊዜ ሰጥተናል። እነዚህን እርምጃዎች እስከምንተገብር ድረስ ያለው ተጠያቂነት የግለሰቦች ነው" ማለታቸውን ጠቅሶ የኬንያው ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል።

ከማክሰኞ ጀምሮ ከ15 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች የፋይዘር ክትባት ሊያገኙ ይችላሉ።