የብራዚል ሕግ አውጪዎች ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ በወንጀል እንዲከሰሱ ድጋፋቸውን ሰጡ

ታትሟል

የብራዚል ሴኔት ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ጃይር ቦልሶናሮ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አያያዛቸውን በተመለከተ ባሳዩት 'እንዝህላልነት' ክስ እንዲመሰረትባቸው ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

አስራ አንድ አባላት ያሉት ኮሚቴ ሰባቱ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጨምሮ ዘጠኝ ክሶች በቦልሶናሮ ላይ እንዲመሰርቱ የሚጠይቀውን ሪፖርት ደግፈዋል።

የኮሚቴው ሰብሳቢ ሴናተር ኦማር አዚዝ ውጤቱን ለብራዚል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይልካሉ።

ቦልሶናሮ "በፍጹም ምንም ጥፋተኛ" አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

በብራዚል ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 መሞታቸው ተረጋግጧል ይህም አሃዝ በሟቾች ቁጥር ከአሜሪካ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።

የኮሚቴው ድምጽ ቦልሶናሮ በወንጀል ስለመጠየቃቸው ማረጋገጫ አይደለም። የሪፖርቱን ምክረ ሃሳብ በፕሬዝዳንቱ የተሾሙት ዋና ዐቃቤ ሕግ ይገመገማል።

ሪፖርቱ ምን ክሶችን ይጠይቃል?

ሪፖርቱ የቦልሶናሮ መንግሥት የኽርድ ኢሙኒቲ (አብዛኛው ሕዝብ በበሽታው ሲያዝ የመከላክል አቅም የሚፈጠርበት መንገድ) የመከላከል አቅምን ለማግኘት በማሰብ ኮሮናቫይረስ አገሪቱን እንዲያንኮታኩት የመፍቀድ ፖሊሲን ተከትለዋል ብሏል።

በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች በተጨማሪ ሌሎች ስምንት ወንጀሎች እንዲከሰሱ ሴኔት ኮሚቴው ምክረ ሃሳብ አቅርቧል። ከእነዚህም መካከል ወንጀልን ማነሳሳት፣ ሰነዶችን ማጭበርበር እና ማኅበራዊ መብቶችን መጣስ ይገኙበታል።

ቦልሶናሮ የሕዝብን ገንዘብ አላግባብ በመጠቀም እና ስለ ወረርሽኙ የውሸት ዜና በማሰራጨትም ተከሰዋል።

ባለ 1 ሺህ 300 ገጹ ሪፖርት በሁለት ኮርፖሬሽኖች እና በሌሎች 77 ሰዎች ላይ ክስ እንዲመሰረት ምክረ ሃሳብ አቅርቧል። ከእነዚህም መካከል ሦስቱ የፕሬዚዳንቱ ልጆች ናቸው።

የሪፖርቱ መሪ የነበሩት ሴናተር ሬናን ካልሃይሮስ ውሳኔውን ተከትሎ "የጃይር ቦልሶናሮ መንግሥት ትርምስ ወደ ታሪክነት የሚገባው የሰው ልጅ ዝቅተኛው ደረጃ ሆኖ ነው" ብለዋል።

በብራዚል መንግሥት ውስጥ ያሉ ቅሌቶችን እና ሙስናዎችን ይፋ ያደረገውን እና ለስድስት ወራት ሲካሄድ የቆየው ምርመራ በድምጽ አሰጣጡ ተጠናቋል።

በሂደቱ ወቅት በሙሉ ቦልሶናሮ መንግሥታቸው ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ "ትክክለኛውን ነገር እንዳደረጉ" አጥብቀው ተናግረዋል። ደጋፊዎቻቸው ምክረ ሃሳቦቹን ሙሉ በሙሉ "በፖለቲካ እና በምርጫ" ምክንያት የተፈጠረ ሲሉ ውድቅ አድርገዋል።

ክሱ ተመሰረተባቸውም አልተመሰረተባቸው ቦልሶናሮ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ባደረጉት ሥራ ስማቸው ተቀባይነታቸው መቀነሱ ምንም ጥርጥር የለውም።

በመጋቢት ወር ብራዚል በ24 ሰዓታት ውስጥ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን ክብረወሰን ካስመዘገበች ከአንድ ቀን በኋላ ብራዚላውያንን ስለ ኮቪድ-19 "ማልቀስ አቁሙ" ማለታቸው ቁጣ ቀስቅሶ ነበር።

በማኅበራዊ ድር አምባ ላይ የተሳሳቱ መረጃዎችን ማሰራጨቱን ቀጥለውበታል። ፕሬዝዳንቱ የኮቪድ-19 ክትባቶች ኤድስ ይፈጥራሉ ሲል የተናገሩበትን ቪዲዮ በፌስቡክ ሰኞ ተወግዷል።

ዩቲዩብ ቪዲዮውን አግዶ የቦልሶናሮን ቻናልን ለአንድ ሳምንት አግዶታል።