ኡጋንዳ ሙስናን ለመቆጣጠር ወላጆችን በተማሪ ልጆቻቸው በኩል ለመከታተል አስባለች

Briefcase full of dollars
ታትሟል

የኡጋንዳ ፀረ ሙስና ባለሥልጣን በአገሪቱ ያለውን የሙስና ችግር ለመቆጣጠር ልጆችን በመጠቀም አዲስ ዘዴን ተግባራዊ እንደሚያደርግ የተቋሙ ኃላፊ ተናገሩ።

የአገሪቱ የፀረ ሙስና መሥሪያ ቤት ኃላፊ የሆኑት ቤቲ ካምያ ለዲፕሎማቶች ተናገሩ ተብሎ እንደተዘገበው ባለሥልጣኗ ወላጆችን በልጆቻቸው በኩል በመከታተል አዲስ የሙስና መቆጣጠሪያ መንገድ እንዳለ አመለክተዋል።

ባለሥልጣኗ በአገሪቱ ያለውን የሙስና ችግር ለመዋጋት አዳዲስ ዘዴዎን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረው ከዚህ ውስጥም ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

የፀረ ሙስና መሥሪያ ቤት ኃላፊዋ ቤቲ ካምያ ይህንን የተናገሩት ለአውሮፓ ሕብረት የዲፕሎማቶች ቡድን ሲሆን በዕቅዳቸው መሠረት አዲስና ፈጠራ የታከለባቸው የሙስና መከላከያ መንገዶች ተግባራዊ እንደሚያደረጉና እነዚህም ወጪ ቆታቢ መንገዶች ናቸው ብለዋል።

ይህ አዲሱ መስናን የመከታተያ መንገድ ትኩረቱን በተማሪ ልጆች ላይ ያደረገ መሆንን ያመለከቱት ኃላፊዋ በተለይ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉ ልጆች ሕገወጥ ገንዘብ ምን እንደሆነ እንዲያውቁና "ወላጆቻቸው ያላቸው ቅንጡ ቤትና መኪና እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች በሚያገኙት ደሞዝ የሚሸፈኑ መሆናቸውን እንዲጠይቁ እንፈልጋልን" ብለዋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ ገንዘብ በሚከፈልባቸው ትምህርት ቤቶች ያሉ መምህራን አስር ዓመት ለሆናቸው ተማሪዎች የአባታቸውን ስም፣ የት እንደሚሰራ፣ የሥራው ኃላፊነት፣ የሚያሽከረክረው መኪና ዋጋ እና የቤታቸውን ፎቶ የሚያሳይ የቤት ሥራ እንዲሰጡ በማድረግ የሙስና ክትትል ለማድረግ እንዳቀዱ ተናግረዋል።

ነገር ግን አንድ ተማሪ ከታዘዘው የቤት ሥራ ላይ የሚገኝን መረጃ ለፀረ ሙስና ባለሥልጣን አሳልፎ መስጠት ይቻላል ወይ የሚለው ጥያቄ ግልጽ መልስ አልተሰጠበትም።

ባለሥልጣኗ አክለውም መሥሪያ ቤታቸው ከአገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ሙስናን በሚመለከት ውይይት እንዲያደርጉ ይበረታታሉ ብለዋል።

በቤቲ ካምያ የሚመራው በኡጋንዳ የመስና ድርጊቶችን የሚቆጣጠረው ተቋም ከአገሪቱ ሙስናንና ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን ለማስወገድ ሥልጣን የተሰጠው ገለልተኛ ተቋም እንደሆነ በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።