ሶርያ ሰደድ እሳት አስነስተዋል ያለቻቸውን 24 ሰዎች በሞት ቀጣች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሶርያ ባለፈው ዓመት ሆነ ብለው ሰደድ እሳት አስነስተዋል ያለቻቸውን 24 ሰዎች በሞት መቅጣቷን አስታወቀች።
በተጨማሪም ሌሎች 11 ሰዎች የእድሜ ልክ እስራት እንዲሁም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ አምስት ታዳጊዎች ደግሞ ከ10 እስከ 12 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
የሶርያ ፍትሕ ሚንስቴር ድርጊቱን "የሽብርተኞች ተግባር" ብሎታል።
አምና መስከረም ላይ በሶርያ ተራራማ አካባቢ ሰደድ እሳት እንዳስነሱ ግለሰቦቹ እንዳመኑ ተገልጿል። በሰደድ እሳቱ ምክንያት ሦስት ሰዎች ሞተዋል።
የሶርያ የእርስ በእርስ ጦርነት እአአ በ2011 ከተጀመረ ወዲህ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ናት። የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ፕሬዝዳንት ባሻር አልአሳድ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በሞት ቀጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የጦር ወንጀል ምርመራ ቡድን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፤ ብዙዎች በፀረ ሽብር ወይም በወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርበው ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሞት ተፈርዶባቸዋል።
ተገቢው የፍርድ ሒደት ሳይካሄድ የተገደሉ ሰዎች እንዳሉ የዓይን እማኞች እንደጠቆሙም ሪፖርቱ ይገልጻል።
አምና ሰደድ እሳቱ ሲነሳ ምክንያቱ መጠኑን ያለፈ ሙቀት ነው ተብሎ ነበር። በእርግጥ በሶርያ መስከረም አካባቢ የተባለው አይነት ከፍተኛ ሙቀት ታይቶ አይታወቅም።
ከሙቀቱ በተጨማሪ የደረቁ እጽዋት እና ሙቀት የተቀላቀለበት ንፋስ ለሰደድ እሳቱ መነሻ ነው ተብሎ ነበር።
የፍትሕ ሚንስቴር እንዳለው፤ አምና ላታኪያ፣ ታሮውስ፣ ሆምስ እና ሀማ በተባሉ ግዛቶች 187 የሰደድ እሳቶች ተነስተዋል።
እነዚህ ሰደድ እሳቶች 280 ከተሞች እና መንደሮች ላይ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን፤ 13,000 ሄክታር የእርሻ መሬት እና 11,000 ሄክታር የደን ይዞታን አውድመዋል።
በምሥራቅ ሜድትራንያን አካባቢ በየዓመቱ ለሚነሳው ሰደድ እሳት ምክንያቱ የአየር ንብረት ለውጥ ነው ተብሏል።
ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ሙቀት ከመጨመሩም ባሻገር እሳት የሚያጭር ደረቅ ንፋስ ያስከትላል።
ዓለማችን ኢንዱስትሪ ወደተስፋፋበት ዘመን ከተሻገረች ወዲህ በ1.2 ሴንቲ ግሬድ ሙቀቷ ጨምሯል። መንግሥታት የካርበን ልቀትን ለመግታት አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰዱ ሙቀቱም ከዚህ በላይ እንደሚጨምር ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።












