ንግሥት ኤልዛቤት ሆስፒታል ገብተው እንደነበር ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ኪንግደሟ ንግሥት ኤልዛቤት ቀዳሚ የህክምና ምርመራ ለማድረግ ረቡዕ ምሽት ሆስፒታል ገብተው እንደነበር የባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት አስታወቀ።
የ95 ዓመቷ ንግሥት ኤልዛቤት ማእከላዊ ለንደን በሚገኝ አንድ የግል ሆስፒታል ውስጥ ህክምናቸውን ተከታትለው ዊንድሰር ወደ ሚገኘው መኖሪያቸው መመለሳቸውን ተገልጿል።
አሁን በመልካም ሁኔታ ላይ ናቸው የተባሉት ንግሥቲቱ ወደ ሰሜን አየርላንድ ለመጓዝ የነበራቸውን እቅድ ሰርዘዋል።
የህክምና ባለሙያዎች ንግሥቲቷ ወደተለመደው ሥራቸው ከመመለሳቸው በፊት ለጥቂት ቀናት እረፍት ማድረግ እንደሚገባቸው መክረዋል ተብሏል።
ሐሙስ ምሽት ስለንግሥቲቱ መግለጫ የሰጠው የባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት እንዳለው "ንግሥቲቱ ረቡዕ ዕለት ወደ ሆስፒታል ያቀኑት የተለመደ ክትትል ለማድረግ ሲሆን ሐሙስ ምሳ ሰዓት አካባቢ ተመልሰዋል፤ መንፈሳቸውም ተነቃቅቷል" ብሏል።
ንግሥቲቱ ወደ ንጉሥ ኤድዋርድ ሰባተኛ ሆስፒታል የተወሰዱት ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ምክንያት እንዳልሆነም ተገልጿል።
ንግሥት ኤልዛቤት ሁለተኛ ሆስፒታል ውስጥ ለህክምና ሲኣሳልፉ ከፈረንጆቹ ከ2013 በኋላ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ማዕከላዊ ለንደን የሚገኘው ንጉሥ ኤድዋርድ ሰባተኛ የግል ሆስፒታል በንጉሣውያን ቤተሰቦች ይዘወተራል። በቅርቡ በሞት የተለዩት የንግሥቲቱ ባለቤትን ጨምሮ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች የሚታከሙት በዚሁ ሆስፒታል ነው።
ንግሥቲቷ ወደ ሰሜን አየርላንድ መሄዳቸውን ትተው ወደ ሆስፒታል ያቀናሉ የሚለው ዜና ጭንቀት እንዳይፈጥር ተሰግቶ ነበር።
ምንም እንኳ ኤልዛቤት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በተሳተፉባቸው ዝግጅቶች ላይ ነቃ ብለው ቢታዩም ዕድሜያቸው ለጤናቸው ስጋት ሊሆን እንደሚችል አያጠርጥርም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ስለ ንግሥቲቱ የጤንነት ሁኔታ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት የተቆጠበው ግላዊ ሕይወታቸውን ለመጠበቅ ነው ተብሏል።
ምንም እንኳ ቤተ-መንግሥቱ ምንም መረጃ ላለመስጠት አስቦ የነበረ ቢሆንም ዘ ሰን የተሰኘው ጋዜጣ ያወጣው ፅሑፍ ነው የቤተ-መንግሥቱን ሰዎች መረጃ እንዲያወጡ ያስገደዳቸው።
ንግሥቲቱ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በርካታ ቦታዎችን እየተዘዋወሩ ሲጎበኙ፤ የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲታደሙ ነበር የከረሙት።
የንግሥት ኤልዛቤት የዕለተ ከዕለት ተግባር መመዝገቢያ እንደሚያሳየው በፈረንጆቹ የጥቅምት ወር ብቻ 16 ዝግጅቶችን ታድመዋል። ይህ ወደ ሰሜን አየርላንድ ሊያደርጉ ያሰቡትን ጉብኝት ሳይጨምር ነው።
ቤተ-መንግሥቱ እንዳለው ንግሥቲቱ ወደ ሰሜን አየርላንድ ለማድረግ ያሰቡት ጉብኝት አለመሳካቱ ቢያበሳጫቸውም የዶክተር ምክርን ሰምተው ዕረፍት እያደረጉ ይገኛሉ።
ንግሥቲቱ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው የግላስጎው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።












