ሩሲያ የኔቶ ዲፕሎማቲክ ተልዕኮዋን ልታቋርጥ መሆኑን ይፋ አደረገች

ታትሟል

ሩሲያ ከኔቶ ጋር ያላትን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ልታቋርጥ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ ተናገሩ።

ከዚህም በተጨማሪ በኔቶ የሞስኮ ቢሮ ያሉ ሠራተኞች የሥራ ፈቃዳቸው ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ እንደሚነጠቅ ተነግሯል።

ይሆ የሆነው ኔቶ በያዝነው ወር መባቻ ስምንት ሩሲያዊያን እንደ መረጃ አቀባይ እየሠሩ ነው ሲል እንዲባረሩ ካደረገ በኋላ ነው።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አሊያም በእንግሊዝኛ ምሕፃረ ቃሉ ኔቶ ከሩሲያ ጋር ያለው ግንኙነት ከጊዜ ጊዜ እየሻከረ መጥቷል።

የሁለቱ ግንኙነት የበለጠ መላላት የጀመረው በፈረንጆቹ 2014 ሩሲያ ክሬሚያን ከዩክሬን ቆርጣ ከወሰደች በኋላ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላቭሮች ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ሩሲያ ከኔቶ ጋር ያላትን ግንኙነት የማቋረጥ እርምጃውን የወሰደችው "የኔቶን ድርጊት ተከትላ ነው።"

ሩሲያ የጦር ጥምረቱ ጉዳዩን በውይይት ከመፍታት ይልቅ እርምጃ መውሰድን መርጧል ስትል ትወቅሳለች።

ሰርጌ ላቭሮቭ "የኔቶ አባል ድርጅቶች አስቸኳይ ነገር ካላቸው ቤልጂዬም ያሉት አምባሳደራችንን ማናገር ይችላሉ" ብለዋል ሲሉ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ከሚኒስትሩ መግለጫ በኋላ ኔቶ የሩሲያን እርምጃ መዝግቦ መያዙን አስታውቋል።

"ይህ መሆኑ ያሳዝነናል" ብለዋል የኔቶ ቃል አቀባይ ኦዋና ሉንጌሹ። አክለውም "ኔቶ በሩሲያ ላይ ያለው አቋም የማይዋዥቅ ነው። ሩሲያ ቁጣ የተሞላበት እርምጃ ብትወስድም እኛ በኔቶ-ሩሲያ ካውንስል በኩል ጉዳዩን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ ነን።"

የጀመርኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄኮ ማስ የሩሲያን እርምጃ አሳሳቢ ሲሉ ገልፀውታል።

"ይህ ጉዳይ የሚያስቆጭ ብቻ አይደለም። ሞስኮ የወሰደችው ውሳኔ ያለን ግንኙነት በጣም የሚጎዳው ነው" ብለዋል ሚኒስትሩ።

ኔቶ ስምንት ሩሲያዊያን ዲፕሎማቶችን ካባረረ በኋላ ብራሰልስ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት በሞስኮ ዲፕሎማቲክ ተልዕኮ ሥር የሰዎች ቁጥር ወደ 10 ወርዷል።

በወቅቱ የኔቶ ዋና ፀሐፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ድርጅታቸው "ከሩሲያዊያን አጠራጣሪ ድርጊት በማየታችን ነው ንቁ ሆነን የጠበቅነው" ብለው እንደነበር አይዘነጋም።

አንድ የኔቶ ባለሥልጣን የተባረሩት ግለሰቦች "ያልታወጀላቸው ሩሲያዊያን ሰላዮች ናቸው" ብለዋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት ሩሲያ ነርቭ የሚያጠቃ መርዝ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ አንድ ሰው ለመግደል ተጠቅማለች በሚል ኔቶ በርካታ ሩሲያዊያንን ከተልዕኮው አባሮ ነበር።