ኮቪድ-19፡ አሜሪካ ሙሉ ክትባት ለወሰዱ ሰዎች የጉዞ እገዳ ልታነሳ መሆኑን አስታወቀች

ታትሟል

አሜሪካ ሙሉ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለወሰዱ 33 አገራት መንገደኞች በዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ ድንበሮቿን እንደምትከፍት አስታወቀች።

በዚህ በዋይት ሐውስ በተዋወቀው አዲሱ ሕግ መሠረት ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ባሉት 72 ሰዓታት ውስጥ ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸው የተረጋገጠ ክትባት የወሰዱ መንገደኞች ወደ አገሪቱ መግባት ይፈቀድላቸዋል።

ውሳኔው አሜሪካ ባለፈው ዓመት የጣለችውን ጥብቅ የጉዞ ገደብ ማብቃቱን ያመላከተ ነው ተብሏል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ "መመሪያው በሕብረተሰብ ጤና የሚመራ፣ ጥብቅ እና ወጥነት ያለው ነው" ብለዋል።

አዲሱ ሕግ 26 የአውሮፓ አገራትን በያዘው ቡድን - ሸንገን አገራት እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)፣ በብራዚል፣ በቻይና፣ በሕንድ፣ በኢራን፣ በአየርላንድ እና በደቡብ አፍሪካ ላይ ተግባራዊ ይሆናል።

በአገሪቷ አሁን ላይ ተግባራዊ እየሆነ ያለው መመሪያ በዩኬ፣ በቻይና፣ በሕንድ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በኢራን፣ በብራዚል እና በበርካታ የአውሮፓ አገራት የሚኖሩ የአሜሪካ ዜጋ ያልሆኑ መንገደኞች ለሚቀጥሉት 14 ቀናት ወደ አገሪቷ እንዳይገቡ ይከለክላል።

ሆኖም በአዲሱ ሕግ ከ150 አገራት አብዛኞቹ ደግሞ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ሲፈተኑ ከነበሩ አገራት ተጓዦች በነጻነት ወደ አሜሪካ መግባት መቀጠላቸው መነጋገሪያ ሆኗል።

ይሁን እንጂ ባለሥልጣናት በአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ከተረጋገጡ ክትባቶች አንዱን የወሰዱ ወይም ደግሞ ለድንገተኛ ጊዜ በዓለም ጤና ድርጅት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተፈቀዱ ክትባቶችን የወሰዱ ሰዎች ከተጠቀሱት አገራት ወደ አሜሪካ ለመግባት ብቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በድንገተኛ ክትባት ረገድም በዩኬ በስፋት የተሰጠውን አስትራዜኒካ ክትባት እንዲሁም የቻይናውን ሲኖቫክ እና ሲኖፋርም ክትባት የወሰዱ ወደ አገሪቷ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል።

መንገደኞች አገሪቷ ሲደርሱ ወደ ለይቶ ማቆያ መግባት እንደማይጠበቅባቸውም ሕጉ ይገልጻል።

አዲሱ ሕግ ከተለያየ የዓለም ክፍል ወደ አሜሪካ በተደጋጋሚ ለሚሄዱ መንገደኞችን ደስታን ፈጥሯል።

ከእነዚህ መካከል በደቡብ ምሥራቅ ኢንግላንድ በምትገኘው ኬንት ከተማ ነዋሪ የሆነው ዳን ጆንሰን ይገኝበታል።

ዳን በአሜሪካ ይኖር የነበረው አባቱ በካንሰር በሽታ ከመሞቱ በፊት ሄዶ መጠየቅ እንዳልቻለ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"አባቴን ለመሰናበትም አልሄድኩም፤ በጉዞ እገዳው ምክንያትም ከ2019 ጀምሮ አላየሁትም፤ ፈታኝ ጊዜ ነበር። ምንም እንኳን እገዳው መነሳቱ ቢዘገይም ያሳደገችኝን እናቴን ማየትና የአባቴ የነበሩ ንብረቶች እንዲደርሷት መርዳት እችላለሁ" ብሏል ዳን።

አርብ ዕለት የተዋወቀው አዲሱ ሕግ ባለፈው መስከረም ወር ላይ ተግባራዊ በነበሩት ለውጦች ላይ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ሆኗል።

የባይደን አስተዳዳር ባለሥልጣናት መጀመሪያ ላይ አዲሱ መመሪያ በአውሮፓውያኑ 'ኅዳር ወር መጀመሪያ' ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀው ነበር። ይህም በርካታ የውጭ መንገደኞች የጉዞ ፕሮግራማቸውን ለማቀድ እርግጠኛ እንዳይሆኑ አድርጓቸው ነበር።

የእንግሊዝ አየር መንገድ - ቨርጂን አትላንቲክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሻይ ዌስ እርምጃውን የተቀበሉ ሲሆን ይህ በዓለም ላይ ያለው የክትባት ሥርጭት ውጤትን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አክለውም "አሁን ላይ ዩኬ ከዋና የኢኮኖሚ አጋሯ አሜሪካ ጋር የንግድና የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ እንዲሁም ወዳጆች፣ ቤተሰቦችና የሥራ ባልደረቦች እንደገና በማገናኘት ግንኙነቷን ማጠናከር ትችላለች" ብለዋል።

አሜሪካ የጉዞ ገደቧን በማንሳት ከብዙ አገራት ወደ ኋላ ቀርታለች። ይህም ከበርካታ አጋሮቿ ጋር አለመግባባትን ፈጥሯል።

ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት በካናዳ እና ሜክሲኮ ጋር በምትገናኝበት የየብስ ድንበሯ ጥላው የነበረው የጉዞ ገደብ ሙሉ ክትባት ለወሰዱ ሰዎች እንደሚነሳ አስታውቀዋል።

ሆኖም ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች አሁንም በየብስ ድንበር መግባት አይፈቀድላቸውም።