ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን አገራቸው 'የማይበገር ሠራዊት' እንደምትገነባ ተናገሩ
አሜሪካ በአገራቸው ላይ ከምትከተለው የጠላትንት ፖሊሲ አንጻር ሰሜን ኮሪያ "የማይበገር ሠራዊት" እንደምትገነባ መሪው ኪም ጆንግ-ኡን መናገራቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ኪም ጆንግ-ኡን ጨምረውም አገራቸው ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያዎችን የምታበለጽገው እራሷን ለመከለከል እንጂ ጦርነት ለመጀመር አይደለም ብለዋል።
ኪም ይህን አስተያት የሰጡት የተለያዩ ትላልቅ ሚሳኤሎች ጭምር በቀረቡበት ባልተለመደ የመከላከያ ኤግዚቢሽን ላይ በተገኙበት ወቅት ነው።
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ አዲስ ናቸው ያለቻቸውን ፀረ-አውሮፕላ ሚሳኤልን ጨምሮ ፈጣን የተባለ ሚሳኤልን ሞክራለች። ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ በቅርቡ ከሰርጓጅ መርከብ የሚወነጨፉ መሳሪያዎችን ሞክራለች።
ኪም በፒዮንግያንግ በተዘጋጀው የመከለከያ ኤግዚቢሽን ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አገራቸው ከጎረቤት ደቡብ ኮሪያ ጋር ወደ ጦርነት መግባት እንደማትሻ ተናግረዋል።
ኪም የአገራቸውን ብሔራዊ ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሲባል ጦርነትን ለማስቀረት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ኪም በንግግራቸው አሜሪካ በደቡብ እና ሰሜን ኮሪያ መካከል ውጥረት እየፈጠረች ነው ሲሉ ከሰዋል።
የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ የገለጸ ሲሆን፤ ፒዮንግያንግ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲላላላት የኒውክለር እንቅስቃሴዋን እንድታቆም በአሜሪካ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦላታል። ሰሜን ኮሪያ ግን በዚህ አትስማማም።
በኤግዚቢሽኑ ላይ ኪም ጆንግ-ኡን የወታደር መለዮ ለብስው እና በሚሳኤሎች ተከበው ሥነ ሥርዓቱን ለሚሳተፉት "ከልብ የመነጨ ኩራት" ተሰምቶኛል ሲሉ ተናግረዋል።
የሰሜን ኮሪያ መሪው ኪም ደቡብ ኮሪያ ጦር መሳሪያዎችን ማበልጸጓን እንደቀጠለች አስታውሰው፣ ሰሜን ኮሪያም ልክ እንደ ደቡብ ኮሪያ ጦሯን የመገንባት መብት አላት ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸውን ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን እና የኒውክሌር መሳሪያዎችን እንዳትሞክር በተባበሩት መንግሥታት ክልከላ ተጥሎባታል።
ሰሜን ኮሪያ ይህን ክልከላ በተደጋጋሚ በመተላለፏ ጠንካራ ማዕቀቦች ተጥሎባት ይገኛል።
ይህ ማዕቀብ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተደማምሮ ሰሜን ኮሪያ በቅርብ ዓመታት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ከቷታል ተብሏል።
የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ ድንበሮቿን በመሉ ዘግታለች። ይህም ዋነኛ ምጣኔ ሀብታዊ አጋሯ ከሆነችው ቻይና ይገቡ የነበሩ ምግብ እና ነዳጅ ሰሜን ኮሪያ መግባት አቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የሰሜን ኮሪያ መሪ ጤና እንደራቃቸው ይገመታል። ኪም ከሰውነታቸው ክብደት ጋር በተያያዘ የጤና መቃወስ ሳያጋጥማቸው አይቀርም ይባላል።
በመቀመጫቸው ደቡብ ኮሪያ ያደረጉ የሰሜን ኮሪያ ተንታኞች ኪም ባለፉት ጥቂት ወራት በከፍተኛ መጠን የሰውነታቸውን ክብደት መቀነስ ችለዋል ይላሉ።