ፌስቡክ አገልግሎቶቹ በድጋሚ ተቋርጠው እንደነበር ተገለጸ

ታትሟል

ፌስቡክ በድጋሚ በአገልግሎቱ ላይ ለተፈጠረው መስተጓጎል ይቅርታ ጠየቀ።

ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ባለፈው ሰኞ መስከረም 24/2014 ዓ.ም ለስድስት ሰዓታት ከተቋረጡ በኋላ በድጋሚ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም መስተጓጎል ገጥሟቸዋል።

ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ላይ የአሠራር ለውጥ በሚደረግበት ወቅት መስተጓጎሉ እንደተፈጠረ ድርጅቱ ገልጿል።

ይህ የአሠራር ለውጥ በመላው ዓለም ያሉ ተጠቃሚዎቹ ላይ ለፈጠረው የአገልግሎት መቆራረጥ ፌስቡክ ይቅርታ ጠይቋል።

ሰኞ የተፈጠረው የአገልግሎት መቋረጥ እና የትላንቱ ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ድርጅቱ ተናግሯል።

ለሁለት ሰዓታት ገደማ አገልግሎታቸው የተቋረጠው ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ሜሴንጀር እና ወርክፕሌስ ናቸው።

"ላለፉት ሁለት ሰዓታት አገልግሎታችንን ማግኘት ባለመቻላችሁ ይቅርታ እንጠይቃለን። የእኛን አገልግሎቶች ተጠቅማችሁ እርስ በእርስ መረጃ እንደምትለዋወጡ እናውቃለን። አሁን ችግሩን ቀርፈነዋል። በዚህ ሳምንት ላሳያችሁን ታጋሽነት እናመሰግናለን" ሲል ድርጅቱ መግለጫ አውጥቷል።

ዳውንዲቴክተር የተባለው የድረ ገጾች መዛኝ ድርጅት እንዳለው፤ ትላንት አርብ ለተወሰኑ ሰዓታት የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች የአገልግሎት መስተጓጎል ገጥሟቸዋል።

የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ጉዳዩን ወደ ትዊተር እና ሌሎችም ማኅበራዊ ገጾች በመውሰድ የፌስቡክ አገልግሎት በድጋሚ በመቋረጡ ቅሬታ ሲያሰሙ ነበር።

ሰኞ ለተፈጠረው የአገልግሎት መቋረጥ ምክንያቱ "የቴክኒክ ጉዳይ" እንደነበር ፌስቡክ መግለጹ ይታወሳል።

ይህ ችግር ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕን ከማቋረጡ ባሻገር የድርጅቱ ሠራተኞችን ኢሜልም ከሥራ ውጪ አድርጓል።