በአፍጋኒስታን መስጊድ ላይ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍጋኒስታኗ ኩንዱዝ ከተማ በሚገኝ መስጊድ ላይ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት 50 ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የአሜሪካ ወታደሮች ከሄዱበት ጊዜ አንስቶ የተፈፀመ አስከፊው ጥቃት መሆኑም ተገልጿል።
የቦምቡ ጥቃት በደረሰበት ሰይድ አባድ መስጊድ የሞቱ ሰዎች አካላት ተበጣጥሰው የታዩ ሲሆን ስፍራውም የሺዓ ሙስሊም ማህበረሰብ የሚያዘወትሩት ነው።
በፍንዳታውም ከ100 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።
ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም ፣ ነገር ግን የአካባቢው እስላማዊ መንግሥት ቡድንን ጨምሮ አክራሪ የሱኒ ሙስሊም አክራሪዎች የሺዓውን ማህበረሰብ ዒላማ አድርገውታል።
ለዚህም ዋነኛ ምክንያታቸው የሺዓ ሙስሊሞችን እንደ መናፍቃን መቁጠራቸው ነው።
ገዥውን ታሊባንን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቃወመው የክልላዊ አጋሩ የኢስላማዊ መንግሥት ቡድን አይኤስ ኬ (IS-K) በቅርቡ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛቶች በርካታ የቦምብ ጥቃቶችን ፈጽሟል።
ከነዚህም መካከል በነሐሴ ወር በካቡል አየር ማረፊያ ላይ ያደረሰው አስከፊ ጥቃት ይገኝበታል።
ቡድኑ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በሺዓ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት በመስጊዶች ፣ በስፖርት ክለቦች እና በትምህርት ቤቶች ላይ አድርሰዋል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ቡድኑ በታሊባን ላይ የማጥቃት ዘመቻውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ዶክተሮች የደም ልገሳ ይፈልጉ እንደሆነ ለመገምገም ወደ ሆስፒታል ያቀኑት የአካባቢው ነጋዴ ዛለማይ አሎክዛይ ምስቅልቅል ትዕይንቶችን ማየታቸውን ገልፀዋል።
"አምቡላንሶች በመስጊዱ ስፍራ በርካታ የሞቱ ሰዎችን ያመላልሱ ነበር" ሲሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።












