በፈረንሳይ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሺዎች የሚቆጠሩ ካህናት በህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሰዋል

ታትሟል

በፈረንሳይ በባለፉት 70 ዓመታት ውስጥ በካቶሊክ ቄሶች 216 ሺህ ያህል ተጎጅዎች የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ መሆናቸው አንድ ምርመራ አጋልጧል።

በፈረንሳይ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሺዎች የሚቆጠሩ ካህናት በህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃትን ፈፅመዋል ሲል በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የደረሱ ጥቃቶችን የሚመረምር ኮሚሽን ኃላፊ ተናግረዋል።

ምርመራው ከአውሮፓውያኑ 1950 ጊዜ ጀምሮ ያለውን ጥቃት ፈትሿል።

ዣን ማርክ ሳውቬ ለፈረንሣይ መገናኛ ብዙኃን እንደገለፁት ኮሚሽኑ ከ 2ሺህ 900 እስከ 3 ሺህ 200 የሚደርሱ ጥቃት ፈፃሚ ካህናትንና ሌሎች የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮችን አግኝቷል።

በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኗ 115 ሺህ 000 ካህናት እና አገልጋዮች አሉ።

ምናልባትም በቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን የተፈፀመው ቁጥር ሲካተት 330 ሺህ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

አንድ የጥቃቱ ሰለባ ሪፖርቱን በፈረንሳይ ታሪክ ውስጥ የለውጥ ምዕራፍ ብሎታል።

አክለውም "ይህ ዝቅተኛው ግምት ነው" ብለዋል።

ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት ረዘም ያለው ሪፖርቱን ያወጣ ሲሆን ይሀም በቤተ ክርስቲያኗ፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ መዛግብት እንዲሁም ከተጎጂዎች ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ ላይ የተመሰረተ ነው።

በሌሎች አገሮች ውስጥ በርካታ ወሲባዊ ቅሌቶችን ተከትሎም ነው የፈረንሳይ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአውሮፓውያኑ 2018 ማጣራቱ የተጀመረው።

ከፍተኛ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት ኮሚሽነሩ ዣን ማርክ ለፈረንሣይ ለ ሞንድ ጋዜጣ እንደተናገሩት ኮሚሸኑ የወንጀል ድርጊት ሊጀመር በሚችልባቸው 22 ጉዳዮች ላይ ለዐቃብያነ ሕግ ማስረጃ ሰጥቷል ብለዋል።

አክለውም ጳጳሳት እና ሌሎች ከፍተኛ የቤተክርስቲያኒቱ ባለሥልጣናት በሕይወት ስላሉ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ክሶች ተነግሯቸዋል በማለት አስረድተዋል።

የኮሚሽኑ አባላት የህክምና ባለሙያዎችን ፣ የታሪክ ጸሐፊዎችን ፣ የማህበራዊ ጥናት ባለሙያዎችን እና የነገረ መለኮት ምሁራንን አካቷል።

ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ በወሰደው በዚህም ምርመራ ከ 6ሺ 500 በላይ ተጎጂዎች እና ምስክሮች ማናገር ችለዋል።የመጨረሻው ሪፖርት 2 ሺህ 500 ገጾች አሉት።

የሮማው ካቶሊክ ህትመት ዘ ታብሌት፣ ክሪስቶፈር ላም ለቢቢሲ እንደገለፁት የደረሱት ጥሰቶች ቤተክርስቲያኒቱን "በ 500 ዓመታት ውስጥ ወደ ትልቁ ቀውስ" አስገብቷታል ብለዋል።

ከቅርብ ወራት በፊትም የሮማው ፖፕ ፍራንሲስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ላይ ከፍተኛ ማሻሻያ በማድረግ ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ ሰፊ ትርጓሜ በመስጠት ቅጣት እንዲጣልባቸው ተወስኗል።

በማሻሻያው መሰረት ወሲባዊ ጥቃት የሚባለው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን መመልመል፣ የህፃናት ወሲብ ቪዲዮዎችን ይዞ መገኘት፣ ወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎችን መሸፋፈን ይገኙበታል።