ለአይኤስ የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮዎች በድምፅ የተረከው ግለሰብ በአሜሪካ ተከሰሰ

አይኤስ

የፎቶው ባለመብት, ISD

ታትሟል

ለእስላማዊ መንግሥት ቡድን የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮዎችን በድምፅ የተረከው አንድ ካናዳዊ ዜጋ በአሜሪካ ክስ ተመስርቶበታል።

ትውልዱ ሳዑዲ አረቢያ የሆነው መሐመድ ከሊፋ ከሁለት አመታት በፊት በሶሪያ ውስጥ በኩርድ በሚመራ ሚሊሻ ከተያዘ በኋላ ለኤፍ.ቢ.አይ ተላልፎ ተሰጥቷል።

አቃብያነ ህግ እንደሚሉት የ38 አመቱ ግለሰብ "ከአመፅ በስተጀርባ ያለው ድምጽ" ነው በማለት አስረድተዋል።

ግለሰቡ ቪዲዮዎችን የመተርጎምና የመተረክ ስራ ለአይኤስ ከመስራቱ በፊት ተዋጊ ነበር ይላሉ።

"ለአሸባሪ ድርጅት የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ" በሚል ክስ በሚቀጥለው ሳምንት በአሜሪካ ፍርድ ቤት ይቀርባል።

መሃመድ ካሊፋ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ከአንድ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ "እሱ ዝቅተኛ ደረጃ ተዋጊ እና የአይኤስ "ድምፅ ብቻ " እንደነበር ተናግሯል።

በቪዲዮው ላይ በገለፃቸውና በተረካቸው አሰቃቂ ትዕይንቶች ውስጥ ምንም ሚና አልነበረኝም ሲልም አጥበቆ ተከራክሯል።

መሀመድ ካሊፋ በአውሮፓውያኑ 2013 ካናዳን ለቆ በሶሪያ ውስጥ የሚገኘውን አይኤስን ተቀላቀለ።

እዚያም የቡድኑ የፕሮፓጋንዳ ቡድን ቁልፍ አባል መሆን ችሏል ይህም "በከፊል የእንግሊዝኛ እና የአረብኛ ተናጋሪ እንደመሆኑ መጠን በቋንቋ ችሎታው" እንደሆነ የአሜሪካ የፍትህ መምሪያ መግለጫ አስታውቋል።

መሀመድ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የዕድሜ ልክ እስራት ይጠብቀዋል።

አንገቶች ሲቀሉና ሌሎች አሰቃቂ ድርጊቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ቡድኑ በሶሪያ እና በኢራቅ ያለውን ተደራሽነት ሲያሰፋ የአይኤስ ዓለም አቀፋዊ የቅጥር እንቅስቃሴ ዋነኛ ገጽታ ነበር።

ነገር ግን ታጣቂዎቹ ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ ግዛታቸውን ማጣት ሲጀምሩ የፕሮፓጋንዳው ጥረት ቀንሷል።