የጀምስ ቦንድ አዲሱ ፊልም በመጀመሪያው ቀን 5 ሚሊዮን ፓውንድ ማስገባቱ ተሰማ

ኖ ታይም ቱ ዳይ ሲመረቅ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

'ኖ ታይም ቱ ዳይ' (No time to die) የተሰኘው የጀምስ ቦንድ አዲሱ ፊልም በዩኬ ቦክስ ኦፊስ የመጀመሪያ ቀን እይታ 5 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ ገቢ አግኝቷል።

የዳንኤል ክሬግ ወይም የጄምስ ቦንድ የመጨረሻው ፊልም እንደሆነ የተነገረለት ''ኖ ታይም ቱ ዳይ' በእንግሊዝ እና በአይሪሽ ሲኒማ ቤቶች በመጀመሪያው ቀን ከ 4.5 እስከ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ሳያስገባ እንዳልቀረ የፊልሙ ፕሮዲውሰሮች ገምተዋል።

ፊልሙ ለእይታ የሚበቃበት ቀን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በተደጋጋሚ የተቀየረ ሲሆን የፊልሙ መውጣት የቦክስ ኦፊስ እይታን በመጨመር ተቀዛቅዞ የቆየውን የፊልም ኢንደስትሪ ወደ ነበረበት እንደ ሚመልሰው እየተጤነ ይገኛል።

ባለፈው ሐሙስ አዲሱን ፊልም የተመለከቱት ሰዎች ቁጥር ከ2015 ተመልካች በ13 በመቶ የበለጡት ቢሆንም በ2012 ጀምስ ቦንድ ያወጣውን 'ስካይፎል'ን ከተመለከቱት በ26 በመቶ ያነሰ እንደሆነ ዩኒቨርሳል ፒክቸርስ የተሰኘው የፊልም ተቋም አስታውቋል።

በተጨማሪም አዲሱ ፊልም በዩኬ "ከማንኛውም ፊልም በላይ በስፋት የተለቀቀ" እንደሆነም ተነግሯል።

'ኖ ታይም ቱ ዳይ' በ 772 ሲኒማ ቤቶች በእንግሊዝ እና በአየርላንድ ሐሙስ ዕለት ለዕይታ መብቃቱን ዩኒቨርሳል ፒከቸርስ ያስታወቀ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ 2019 ከታየው 'Star Wars: Rise of Skywalker' ከታየባቸው የሲኒማ ቤቶች ብዛት በ25 እንደሚልቅ ተነግሮለታል።

ይህ ፊልም ለእይታ በሚበቃበት ሳምንት ከጠቅላላው የዩኬ እና የአየርላንድ ቦክስ ኦፊስ 92 በመቶን እንደሚይዝ 'ጉወር ስትሪት አናሊቲስ' የተሰኘ የፊልም ቴክኖሎጂ ኩባንያ ተንብዮ ነበር።

በዩናይትድ ኪንግደም እና በአየርላንድ ውስጥ ከ 30,000 በላይ ሰዎች የታደሙ ሲሆን ፊልሙ ለእየታ ከበቃ በኋላ ያሉትን አራት ቀናት 1.6 ሚሊዮን ተመልካቾች ቅድሚያ ተኬት መግዛታቸው ተነግሯል።