ኮቪድ-19፡ አውስትራሊያ ከ18 ወራት በኋላ ዓለም አቀፍ ድንበሮቿን ልትከፍት ነው

ታትሟል

አውስትራሊያ ከ18 ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ለተከተቡ ተጓዦች ዓለም አቀፍ ድንበሯን ክፍት እንደምታደርግ አስታወቀች።

አውስትራሊያ ከአንድ ወር በኋላ ከኮሮናቫይረስ ነፃ የሆኑ የአገሪቱ ዜጎች እና ዘመዶቻቸው ብቻ የአገሪቱን ድንበር አቋርጠው እንዲገቡ እንደምትፈቅድ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት አውስትራሊያ ድንበሯን ለውጪ አገራት ተጓዦች ክፍት ባታደርግም፤ ወደ ፊት ጎብኚዎች ወደ አውስትራሊያ እንዲመጡ ይፈቀዳል ተብሏል።

አውስትራሊያ ተግብራው የነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥብቅ መመሪያ የኮቪድን ጫና ለማቃለል አግዟል ቢባልም ቤተሰቦች እንዲራራቁ ምክንያት ሆኗል የሚል ትችት ይቀርብበታል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የክትባት ሽፋናቸው ከ80% በላይ የሆኑ ግዛቶች የጉዞ እገዳቸው እንደሚነሳላቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስትራሊያዊያን ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው የሚመለሱበት ጊዜ ነው ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን ወደ አውስትራሊያ የሚገባ እያንዳንዱ ተጓዥ እስከ 3,000 የአውስትራሊያ ዶላር ያስወጣ የነበረው አስገዳጅ የ14 ቀናት የሆቴል ቆይታ እንደሚነሳም አክለዋል።

አሁን ላይ መመሪያው ተጓዦች ለ7 ቀናት በቤታቸው ይቆዩ በሚል አስገዳጅ ሕግ ተቀይሯል።

ይህ የአውስትራሊያ ውሳኔ የበረራ ፍላጎቶችን ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፤ ይሁን እንጂ አየር መንገዶች በረራዎችን በፍጥነት ለመጀመር እና ሙሉ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ እንዳልሆኑ አስታውቀዋል።

በወረርሽኙ ምክንያት ሲድኒ፣ ሜልቦርን እና ካንቤራ የተባሉት የአገሪቱ ታላላቅ ከተሞች በአሁኑ ጊዜ በእንቅስቃሴ ገደብ ሥር ይገኛሉ።

የአውስትራሊያ ጥብቅ የድንበር ፖሊሲ በተለይ በወረርሽኙ መጀመሪያ ላይ አገሪቱ የቫይረሱን ሥርጭት ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድትቆጣጠር አግዞ ነበር። ዴልታ የተሰኘው የቫይረሱ አዲስ ዝርያ ግን አውስትራሊያን ሌላ ፈተና ውስጥ ከትቶ ነበር።