ዩናይትድ አየር መንገድ የማይከተቡ ሠራተኞቹን ሊያባርር ነው

ታትሟል

ወደ 600 የሚጠጉ የዩናይትድ አየር መንገድ ሠራተኞች የኩባንያውን የኮቪድ -19 ክትባት ፖሊሲን ባለማክበራቸው ከሥራ ሊባረሩ ነው።

አብዛኛዎቹ 67 ሺህ አሜሪካ መቀመጫቸውን ያደረጉ ሰራተኞች ተከትበው ሰርቲፊኬታቸውን ተቀብለዋል፤ ሰራተኞቹ ስለመከተባቸው ማስረጃቸውን በያዝነው ሳምንት ሰኞ ማሳየት ነበረባቸው።

"በጣም አስቸጋሪ ውሳኔ ላይ ነው የደረስነው" በማለት ኃላፊው ለሰራተኞቻቸው ማሳወቃቸው ተነግሯል።

በቺካጎ መቀመጫውን ያደረገው አየር መንገድ በነሐሴ ወር የኮቪድ-19 ክትባት ለሠራተኞቹ አስገዳጅ አድርጓል።

በአሜሪካ የሚገኙ የአየር መንገድ ሠራተኞቹ የክትባት ማስረጃቻውን በኦንላይን መጫን ፣ ወይም ሁለት ጊዜ መከተባቸውን የሚያረጋግጥ ወረቀት በተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ እስከ ሰኞ ማምጣት ነበረባቸው።

በሃይማኖታዊ ወይም በሕክምናም ሆነ በሌላ ምክንያቶች የኮሮናቫይረስ ክትባት አንከተብም በማለት አሻፈረኝ ያሉ 593 ሠራተኞች ሥራቸውን ያጣሉ።

"በአሜሪካ ላሉት ሁሉም ሠራተኞች እንዲከተቡ የጠየቅንበት ምክንያት ቀላል ነበር ፤የ ህዝባችንን ደህንነት ለመጠበቅ። እና እውነታው ይህ ነው ። ሁሉም ሰው ሲከተብ የሁሉም ሰው ደህንነቱ የተጠበቀ ይሆናል። ክትባትንም አስገዳጅ ያደረግነው በዚህ ሁኔታ ነው" በማለት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ስኮት ኪርቢ እና ፕሬዝዳንቱ ብሬት ሃርት ተናግረዋል።

"ይህ በማይታመን ሁኔታ ከባድ ውሳኔ ነበር ነገር ግን የሰራተኞችን ደህንነት መጠበቅ ሁል ጊዜ ቀዳሚ ተግባራችን ነው" ብለዋል።

ሆኖም ከእነዚህ ሠራተኞች መካከል አንዳንዶቹ ከተከተቡና በቀላሉ የክትባት ማስረጃ ማቅረብ ካልቻሉ ወይም በጉዳዩ ላይ ከመደበኛ ስብሰባዎች በፊት ከተከተቡ ሊቆዩ ይችላሉ ብሏል ኩባንያው።

ዩናይትድ የሚያባርራቸውን ሰራተኞች በተመለከተ በማህበር ስምምነቶች ውስጥ የተዘረዘሩትን ህጎች እከተላለሁ ብሏል። ነገር ግን የስራ ማባረሩ ሂደት ሳምንታት ወይም ወራት ሊወስድ እንደሚችልም ተነግሯል።

ተጨማሪ 2 ሺህ ሠራተኞቹ የክትባት ፖሊሲው ተግባራዊ እንዳይደረግባቸው ጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም በጊዜያዊነት ከዚህ ፖሊሲ ነፃ የሚሆኑትን ከጥቅምት ጀምሮ ያልተከፈለ እረፍት እንደሚሰጥ ገልጾ ነበር።

ነገር ግን ፖሊሲውን የተቃወሙ ስድስት ሰራተኞች ክስ ካቀረቡ በኋላ እንዲቆም ተደርጓል።