ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ሥራቸውን መልቀቃቸውን አሳወቁ
የኢትዮጵያ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቃቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጻፉት ደብዳቤ አሳወቁ።
ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰራጩት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸው ቅጂ ላይ "በህሊናዬ ላይ ጫናን በሚያሳርፉ ግላዊ ባህርይ" ባሏቸው ምክንያቶች ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በሚገልጸው ደብዳቤ ላይ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ስለሚኒስትሯ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ከሚኒስቴሩ የኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር እንዳረጋገጠው ፊልሰን አብዱላሂ ደብዳቤው የራሳቸው መሆኑንና ምክንያታቸውም በደብዳቤው ላይ መስፈሩን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ በደብዳቤያቸው ላይ ከሥራቸው ለመልቀቅ ምክንያታቸውን በግልጽ ባያስቀምጡም፤ "ከእሴቶቼና ከታማኝነቴ ጋር ተቃራኒ የሆኑና ሥነ ምግባሬን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ነገሮች፤ እንዲሁም እነዚህን እምነቶች መካድ የእራሴንና የዜጎቻችንን እምነት መጣስ በመሆኑ ነው" ብለዋል።
ጨምረውም እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በአገራዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ተከትሎ መሆኑን ቢጠቅሱም ምንም አይነት ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቢቢሲ ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስላሰራጩት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ከራሳቸው ለማረጋገጥና ዝርዝር ለማወቅ ጥረት ቢያደርግም ለስልክ ጥሪውና ለአጭር የጽሁፍ መልዕክቱ ምላሽ አላገኘም።
ቢቢሲ ያናገራቸው በሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር የሆኑት አቶ ዘላለም ሻምበል ስለሚኒስትሯ ሥራ መልቀቅ በተመለከተ ቀደም ብለው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረው ሚኒስትሯን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዜናውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንደተመለከቱና ሁኔታው ያልተጠበቀ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘላለም ዕለቱ በዓል ከመሆኑ አንጻር ዝርዝር መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቆየት ብለውም ከሚኒስትሯ ጋር በስልክ መነጋገራቸውንና የሥራ መልቀቂያው ከራሳቸው የወጣ መሆኑን ምክንያታቸውም በደብዳቤው ላይ የተገለጸው መሆኑን እንደነገሯቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ፊልሰን መጋቢት 03/2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕጩነት ቀርበው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው ከጸደቀው ሴት ሚኒስትሮች መካከል ከወጣቶቹ አንዷ ነበሩ።
ፊልሰን አብዱላሂ በሚኒስትርነት ከመሾማቸው በፊት በማኅበረሰቦች መካከል መግባባትን ለመፍጠር የሚሰራ የቴሌቪዥን ጣቢያን መስርተው ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሚኒስትሯ በደብዳቤያቸው ላይ ውስን የሰው ኃይልና በጀት የነበረው እንዲሁም እምብዛም አገልገሎት እየሰጠ ያልነበረውን መሥሪያ ቤትን በመሪነት በመያዝ ተጨባጭ ውጤቶችን ማምጣት መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
"ምንም እንኳን ጥሩ ያልሆኑ አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ቢኖሩም ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ውጤት ማምጣታችንን በኩራት እናገራለሁ" ብለዋል።
ሚኒስትር ፊልሰን በዚህ ቆይታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ከተለያዩ አጋር ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በማስተዋወቅ በኢትዮጵያ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጣል ብለው ያመኑበትን አዲስ ተቋም ለመገንባት፣ ዘዴዎችና ፖሊሲዎችን በመቅረጽ የ10 ዓመት እቅድ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
"እነዚህንም እቅዶች መተግበር ለረዥም ጊዜ ሳይሰራበት የቆየውን የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶችን መብትና ደኅንነት ያሳድጋል። በተለይ ደግሞ አሁን አገሪቷ ባለችበት በዚህ ወቅት በጣም ወሳኝ ነው" ብለዋል።
ሚኒስትሯ በመጨረሻም ለተሰጣቸው እድል ጠቅላይ ሚኒስትሩን አመስግነው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ማገልገል ለእርሳቸው ክብር እንደነበር በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።
ወጣቷ ሚኒስትር በደብዳቤያቸው ላይ እንዳመለከቱት የሥራ መልቀቂያቸው ከሰኞ መስከረም 17/2014 ዓ.ም እንደሆነ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በካቢኔያቸው ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴት ሚኒስተሮችን ያካተቱ ሲሆን ሚኒስትር ፊልሰንም ከእነዚህ መካከል አንዷ ነበሩ።
በመጪው ሰኞ አዲሱ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ሲመሰረት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰይም ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስሩም የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበው ያሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል።