በጀርመን በተካሄደው ምርጫ የአንጌላ ሜርክል ፓርቲ ተሸነፈ

ከፍተኛውን ድምጽ ያገኘው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪ ኦላፍ ሾልትስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከፍተኛውን ድምጽ ያገኘው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪ ኦላፍ ሾልትስ
ታትሟል

የጀርመኑ ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የመራሄተ መንግሥቷ አጌላ ሜርክልን ፓርቲ በጠባብ ውጤት ማሸነፉን ቀዳሚ የምርጫ ውጤቶች አመላከቱ።

ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ 25.7 በመቶውን ድምጽ ሲያገኝ ገዢው ወግ አጥባቂው ፓርቲ ደግሞ 24.1 በመቶ ድምጽ አግኝቷል። የግሪን ፓርቲ በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን 14̇ በመቶ ድምጽ ማግኘቱም አነጋጋሪ ሆኗል።

በቀጣይም መንግሥት ለመመስረት የሚያስፈልገውን አብላጫ ድምጽ አንድ ፓርቲ ባለማግኘቱ ፓርቲዎቹ ጥምር መንግሥት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

ምርጫው ከጅማሮው ውጤቱን ለመገመት የሚያስቸግር መሆኑን በርካቶች ሲናገሩ ነበር። ጥምር መንግሥት በቀላሉ መመስረት የሚቻል እንዳልሆነም ተንታኞች እየገለጹ ይገኛሉ።

ጥምር መንግሥት እስከሚመሰረት ድረስ ተሰናባቿ መራሄተ መንግሥት ሜርክል በሥልጣናቸው ላይ መቀጠላቸው አይቀሬ ነው። ይህም እስከ መጪው ጥር ወር ድረስ ሊቆይ ይችላል።

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት በአውሮፓ የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችውን ጀርመን ለቀጣይ አራት ዓመታት በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳን በዋናነት በመያዝ ይመራል።

ከፍተኛውን ድምጽ ያገኘው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪ ኦላፍ ሾልትስ በቴሌቪዢን በተላለፈ ንግግራቸው መራጮች "ለጀርመን መልካም ብሎም ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ መንግሥት" የመመስረት ሥራ ሰጥተውኛል ሲሉ ተደምጠዋል።

የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪው በበኩላቸው ጥምር መንግሥትን የመመስረት እንዲሁም ያሸነፈው ሁሉንም ጠቅልሎ የማይወስድበት ሂደት ነው ሲሉ ሾልትስን የሚቃረን ንግግር አድርገዋል።

የሊበራል እና የግሪን ፓርቲዎች ከ30 ዓመት በታች ባሉ ወጣቶች ዘንድ ዝነኛ ናቸው። ጥምር መንግሥት ሊመሰረት የሚችለውም በእነዚህ ሁለት ፓርቲዎች አማካኝነት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ።

ውጤቱን ተከትሎም አራት የተለያዩ የጥምር መንግሥት አማራጮች የቀረቡ ሲሆን የመጀመሪያው አማራጭ "የትራፊክ መብራት" ቀለሞችን የያዘ ነው።

የሶሻል ዴሞክራቶችን ቀይ ቀለም፣ የኤፍዲፒን ቢጫ እንዲሁም የግሪን ፓርቲ አረንጓዴ የያዘ የጥምረት አማራጭ ነው።

ሁተኛው "ጃማይካ" የተሰኘው አማራጭ ሲሆን ይህም የጃማይካን ባንዲራ ቀለሞች ያያዙትን ሦስቱን ፓርቲዎች የያዘ ጥምረት ነው። ሾሳል ዴሞክራቶችን፣ ኤፍዲፒን እንዲሁም ግሪን ፓርቲን።

ይህ በጀርመን ታሪክ ሦስት አማራጮችን የቀረቡበት የጥምር መንግሥት የመመስረት ሂደት መሆኑ ተነግሯል።