ታሊባን ወንጀለኞች መቀጣጫ እንዲሆኑ በሚል የአደባባይ ስቅላት ጀመረ

የታሊባን ታጣቂዎች በሔራት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ታሊባን ወንጀለኞች መቀጣጫ እንዲሆኑ በሚል በአንዳንድ ከተሞች ሰዎችን በስቅላት መቅጣት ጀመረ፡፡

ታሊባን እንዳስታወቀው በአፍጋን፣ ሐራት በምትባል ከተማ አንድን ነጋዴ አፍነው ጠልፈው ያገቱ አራት ሰዎችን ገድሎ ሬሳቸውን በከተማዋ ልዩ ልዩ አደባባዮች ሰቅሎታል፡፡

ይህ ድርጊት ተፈጻሚ የሆነው አንድ ሞገደኛ የታሊባን አመራር ከዚህ ወዲያ ጥብቅ ቅጣቶች ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ካስጠነቀቀ ከአንድ ቀን በኋላ ነው፡፡

እነዚህ የአጋቾች ናቸው የተባሉ ሬሳቸው አደባባይ ላይ የተሰቀሉት ወንጀለኞቹ አንድን ነጋዴ ከወንድ ልጁ ጋር አፍነው ለመውሰድና ለማገት በመሞከራቸው ነው ተብሏል፡፡

ሞገደኛ የሚባሉ አንድ የታሊባን ባለሥልጣን ‹ከእንግዲህ ቀልድ የለም፣ የወንጀለኞችን እጅ እንቆርጣለን፣ የሞት ቅጣትም እንጀምራለን› ሲሉ ከአንድ ቀን በፊት ሕዝቡን አስጠንቅቀው ነበር፡፡

የሐራት ከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት የሟቾቹ አስክሬን ወደ ከተማዋ ከመጣ በኋላ በከተማዋ ዋንኛ አደባባዮች በክሬን ታግዞ ተሰቅሏል፡፡

ዋዚሀር አሕመድ የተባለ አንድ የሱቅ ነጋዴ የዓይን እማኝ ለአሶሲየትድ ፕሬስ እንዳብራራው ‹‹አራቱ አስክሬኖች ወደ ሐራት ከተማ ከመጡ በኋላ አንዱ በዋና አደባባዩ ላይ በክሬን ታግዞ ተሰቀለ፡፡ ሌሎቹ ሦስቱ አስክሬኖች ደግሞ ወደ ሌሎች አደባባዮች ተወሰዱ፡፡››

የሐራት ከተማ ምክትል ገዥ ሟልዋይ ሻይር እንዳሉት ይህ የአደባባይ ስቅላት የተፈጸመው ሌሎች ወንጀለኞች ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጽሙ መቀጣጫ እንዲሆኑ ነው፡፡ አፈናና ጠለፋንም ለማስቀረት ነው፡፡

ምክትል ገዥው ጨምረው እንዳረጋገጡት አራቱ ወንጀለኞች ነጋዴውንና ወንድ ልጁን አፍነው ከወሰዱ በኋላ በተደረገ የተኩስ ለውውጥ ነው የተገደሉት፡፡

ታጋቾቹ አባትና ልጅ ደግሞ ነጻ ወጥተዋል፡፡

ቢቢሲ ይህን ክስተት ከገለልተኛ ወገን ማጣራት ባይችልም የወንጀለኞቹ ናቸው የተባሉት ግለሰቦች አስክሬኖች ግን ምሥሎቻቸው በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ሲጋሩ ነበር፡፡

ከአስክሬኖቹ አንዱ በአደባባይ ከተሰቀለ በኋላ ደረቱ ላይ ‹አጋቾች እጣ ፈንታቸው ይህ ነው› የሚል መልእክት የያዘ ጽሑፍ ተለጥፎበታል፡፡

ታሊባን በነሐሴ 15 ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ ለዘብተኛ የአስተዳደር ዘዬን እንደሚከተል ቃል ገብቶ ነበር፡፡

በታሊባን አመራር ውስጥ ሞገደኛ የሚባሉትና ቀድሞ የሃይማኖት ፖሊስ የነበሩት ሙላህ ኑሩዲን ቱራቢ አሁን የእስር ቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ተደርገዋል፡፡

እሳቸው በግልጽ እንዳስታወቁት ስቅላትና እጅን በቅጣት መቁረጥ በታሊባን አስተዳደር የሚቀጥል ተግባር ነው፡፡ ይህም የሚደረገው የሕዝብን ደኅንነትና ሰላም ለማስጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

ሙላህ ከአሶሲየትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህ ዓይነቱ ቅጣት ሲፈጸም ግን እንደ ቀድሞው የታሊባን የአምስት ዓመታት የአስተዳደር ዘመን በስታዲየም ውስጥ ወይም በሕዝብ አደባባዮች አይደረግም ብለው ነበር፡፡

ሆኖም ሙላህ ጨምረው ሲያስገነዝቡ፣ ‹ማንም ሰው ሕግና ቅጣታችን ምን መምሰል እንዳለበት ሊነግረን አይችልም፣ እኛም ስለነሱ እንደማንናገረው ሁሉ› ብለዋል፡፡