የኪም ጆንግ-ኡን እህት ሰሜን ኮሪያ ለንግግር ዝግጁ ልትሆን ትችላለች አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን እህት ኪም ዮ-ጆንግ ደቡብ ኮሪያ "ጠብ አጫሪ" ፖሊሲዋን የምታቆም ከሆነ ለንግግር ዝግጁ ነን አሉ።
ተጽእኖ ፈጣሪዋ ኪም ዮ-ጆንግ ይህን ማለታቸው የተሰማው የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት የኮሪያ ጦርነት እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው።
ሁለቱ ኮሪያዎችን እአአ 1953 ላይ ጦርነት ለማቆም ቢስማሙም የሰላም ስምምነት ላይ ግን አልደረሱም።
ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ጦርነት ሊባል በሚችል ሁኔታ ውስጥ ቆይተዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ሙን ጄ-ኢን ሁለቱ ኮሪያዎች እና አጋሮቻቸው በቀጠናው ሰላም እንዲያወርዱ ጥሪ አቅርበው ነበር።
የደቡብ ኮሪያ አጋር የሆነችው አሜሪካ እንዲሁም የሰሜን ኮሪያ የምጣኔ ሃብት አጋር የሆነችው ቻይና ናቸው ከደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ጥሪ የቀረበላቸው።
ጥሪውን የሰሜን ኮሪያ መሪዎች ውድቅ ቢያደርጉም ዘግይቶ ግን የኪም ጆንግ-ኡን እህት ሰሜን ኮሪያ ለውይይት ዝግጁ ልትሆን እንደምትችል አስታውቀዋል።
ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ልትነጋገር የምትችለው፤ ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰሜን ኮሪያን የተመለከቱ የደቡብ ኮሪያ ፖሊሲዎች ውድቅ ሲደረጉ ነው በማለት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።

ደቡብ ኮሪያ ለ70 ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት መቋጨትን ባለፉት 5 ዓመታት ዋነኛው አጀንዳዋ አድርጋ ቆይታለች። ፕሬዝደንት ሙን ከሦስት ወራት በኋላ የስልጣን ዘመናቸው ከመጠናቀቁ በፊት በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ሰላም ማውረድ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ነው።
ፕሬዝደንቱ ከዚህ ቀደም ሰላም ለማውረድ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ከሳምንታት በፊት ደቡብ ኮሪያ ባህር ሰርጓጅ ባሊስቲክ ሚሳኤል ለሙከራ ማስወንጨፏን ተከትሎ በሰዓታት ልዩነት ሰሜን ኮሪያም የራሷን መሳሪያ ለሙከራ ተኩሳለች።
ከዚህ በተጨማሪም ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር የምታደርጋቸውን ጥምር ወታደራዊ ልምምዶችን አጥብቃ ስትቃወም ቆይታለች። ተጥሎባት የሚገኘው ማዕቀብ እንዲነሳም ትጠይቃለች።
የደቡብ ኮሪያ አጋር የሆነችው አሜሪካ ግን ሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር ጦር መሳሪዎቿን ሳታስወግድ የተጣለባት ማዕቀብ አይነሳም ትላለች።












