ጀርመን ውስጥ ጭምብል እንዲያደርግ የተጠየቀ ግለሰብ በጥይት ሰው ገደለ

ታትሟል

ጀርመን ውስጥ አንድ ግለሰብ ነዳጅ ማደያ ውስጥ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርግ የጠየቀውን ገንዘብ ተቀባይ ተኩሶ መግደሉ ተነገረ።

ግድያውን የፈጸመው ግለሰብ ለዚህ ድርጊት ያበቃው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሐሰት ነው ከሚሉ የሴራ አመለካከት አራማጆችና ከአክራሪ ቀኝ ዘመም ቡድን ጋር ባለው ግንኙነት ሰበብ መሆኑ ተገልጿል።

ግለሰቡ ባለፈው ቅዳሜ በአንድ ነዳጅ ማደያ ውስጥ ጭምብል ባለማድረጉ ውዝግብ ከተነሳ በኋላ መሳሪያ ይዞ ተመልሶ በመምጣት ነው የ20 ዓመቱን ገንዘብ ተቀባይ ተኩሶ የገደለው።

ይህ ግድያም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ጀርመን ውስጥ ከተጣለው ደንብ ጋር በተያያዘ የተፈጸመ የመጀመሪያው የግድያ ወንጀል ነው ተብሏል።

መርማሪዎች ግድያውን የፈጸመው ተጠርጣሪ ማርዮ ኤን የሚባል ግለሰብ መሆኑንና የአክራሪ ቀኝ ዘመም ቡድን ደጋፊ እንዲሁም ኮሮናቫይረስ የለም የሚል እምነት ያለው እንደሆነ ገልጸዋል።

የ49 ዓመቱ ግለሰብ ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ እሁድ ዕለት አይዳር ኦበርስታይን ውስጥ ወደ ሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ እጁን መስጠቱ ተዘግቧል።

በጥቃቱ የተገደለው የነዳጅ ማደያው ገንዘብ ተቀባይ ማንነት ግን በፖሊስ አልተገለጸም፤ ነገር ግን ተማሪ መሆኑ ተነግሯል።

ዐቃቤ ሕጎች እንዳሉት ተጥርጣሪው ወደ ነዳጅ ማደያው ቢራ ለመግዛት አቅንቶ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ባለማድረጉ አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ ተመልሶ ሄዶ ነበር።

ነገር ግን ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ተመልሶ ሲመጣ ጭምብል አድርጎ የነበረ ቢሆንም ጭምብሉን አውልቆ ከገንዘብ ተቀባዩ ጋር በድጋሚ ጭቅጭቅ በማስነሳት ጥይት ተኩሶ ጭንቅላቱን በመምታት ግድያውን ፈጽሟል።

ተንታኞች ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ የተጠርጣሪውን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ በሚፈትሹበት ጊዜ የአየር ንበረት ለውጥ ሐሰተኛ መሆኑን የሚገልጹ ጽሁፎችን የሚያሰራጭ መሆኑን፣ የቀኝ ዘመም አክራሪ ፓርቲ ደጋፊ መሆኑንና "ቀጣዩን ጦርነት በጉጉት እየጠበቅኩ ነው" የሚል ጽሁፍ እንዳሰፈረ አረጋግጠዋል።

የጀርመን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ግድያው በቀኝ ዘመም አክራሪዎችና የሴራ አመለካከት አራማጆች በሚጠቀሙባቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ውይይት መድረኮች ላይ ሲወደስ ነበር።

በምሥራቃዊዋ የቱሪንጊያ ግዛት ውስጥ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የሆኑት ስቴፈን ክራመር እንዳስጠነቀቁት በዕለት ከዕለት ሕይወት ውስጥ የሚጋጥሙ ጥቃቶች እየጨመሩ ነው።

አንድ የጥናት ተቋም እንዳለው የኮሮናቫይረስ በተከሰተበት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የሴራ አመለካከት አራማጆች በሌሎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ተበረታተዋል።

በዚህም ምክንያት ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት መሰንዘርና ክትባት በመስጠት ተግባር ውስጥ የተሰማሩ ዶክተሮችን የማስፈራራት ድርጊት መፈጸማቸውም ተነግሯል።

ለረጅም ዓመታት ጀርመንን በመራሄተ መንግሥትነት የመሩትን አንጌላ ሜርክልን ለመተካት ከሚፈካከሩት ዕጩዎች መካከል ዋነኞቹ በተፈጸመው ግድያ በእጅጉ መደንገጣቸውን ገልጸዋል።