አሜሪካ የሃይቲ ስደተኞችን መመለሷ ቁጣን አስከተለ

የሃይቲ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ካለፈው ቅዳሜ እና ዕሁድ ጀምሮ አሜሪካ በስደተኞች ከተጥለቀለቀው የቴክሳስ ግዛት ወደ ሃይቲ ስደተኞችን ማመላለስ መጀመሯን ተከትሎ በሃይቲ አየር ማረፊያ የደረሱ ስደተኞች ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ስደተኞቹ ከቴክሳስ ሲነሱ ወደ ሃይቲ እየተመለሱ እንደሆነ እንዳልተነገራቸው ሪፖርቶች አመላክተዋል።

በሃይቲ አየር ማረፊያ ሲደርሱም አንድ ግለሰብ ወደ አውሮፕላኑ ተመልሶ ለመግባት ያደረገውን ጥረት ተከትሎ ግርግር ተከስቷል። የበረራው ሰራተኞች የአውሮፕላኑን በር መዝጋታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ትላንት ማክሰኞም ስደተኞች ወደ ሃይቲ ወዳደረሳቸው አውሮፕላን ተመልሰው ለመግባት ሲረባረቡ እንዲሁም ጫማዎችን ሲወረውሩ ታይተዋል።

ስደተኞቹ ከአውሮፕላኑ የተወረወሩ ሻንጣዎቻቸውን ለመሰብሰብ ሲረባረቡ ከአየር ማረፊያው የወጡ ቪዲዮዎች ያሳያሉ።

የአሜሪካ የአገር ውስጥ ባለስጣን እንዳለው በዕለቱ ሁለት የተለያዩ ክስተቶች ተመዝግበዋል።

ኤንቢሲ የተሰኘው የአሜሪካ ሚዲያ ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው ወደ ሃይቲ ከደረሱት በረራዎች በአንዱ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ አንድ የአሜሪካ የስደኞች ጉዳይ ሰራተኛ ላይ ጉዳት ደርሷል።

አንዲሁም ወደ አገራቸው ሊመለሱ እንደሆነ ያወቁ ሃይቲያዊያን በቴክሳስ ከድንበር ጠባቂዎች ጋር መፋለማቸው ሪፖርት ተደርጓል።

በወቅቱ ስደተኞቹ ከብራውንስቪሌ ከተማ ወደ ዴል ሪዮ በአውቶብስ ተጭነው እየተጓዙ ነበር።

«ስደተኞቹ ወደ ሃይቲ እየተመለሱ እንደሆነ በተረዱ ግዜ አውቶብሱን በጉልበት በመንጠቅ ጠፍተዋል» ሲሉ የአሜሪካ ድንበር ተቆጣጣሪ መስሪያቤት ፕሬዘዳንት የሆኑት ብራንደን ጁድ ትላንት ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የስደተኞቹ መመለስ ጉዳይ የተለያዩ ወቀሳዎችን እያስተናገደ ሲሆን ፓርትነርስ ኢን ኸልዝ የተሰኘ በሃይቲ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ተቐም ድርጊቱን « ለማሰብ የሚከብድ ጭካኔ» ሲል ገልጾታል።

«ለሃይቲ ይህ ፈታኝ እንዲሁም አደገኛ ግዜ ነው። በዚህ ግዜ ወንዶችን፣ ሴቶችን እንዲሁም ልጆችን ከዚህ በኋላ ቤታችን ብለው እንኳን ብለው ወደማይጠሯት ሃይቲ መመለስ ጭካኔ ነው» ሲልም ተቐሙ ተቃውሞውን ገልጿል።

የአሜሪካ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ባላስልጣን እንዳለው እስካሁን ድረስ 4000 የሚጠጉ ስደተኞች ወይ መጡበት ተመልሰዋል አልያም ጥያቄያቸው እስከሚታይ ድረስ ወደሌሎች ማቆያዎች ተወስደዋል።