ከመቅደላ በዝርፊያ የተወሰዱና ከጨረታ ድርጅት የተገዙ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ሊመለሱ ነው

ታትሟል

ከመቅደላ በዝርፊያ ወደ እንግሊዝ የተወሰዱና ከጨረታ ድርጅትና ከግለሰቦች የተገዙ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ሊመለሱ መሆኑን በእንግሊዝ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

ቅርሶቹ መስቀል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ጋሻን የሚያካትት ሲሆን ቅርሶቹንም ገዝቶ ለኤምባሲው ያስረከበው ሻሃራዛድ የተባለ ፋውንዴሽን ነው።

ተቋሙ ቅርሶቹን እንግሊዝ ከሚገኝ አንድ የጨረታ ድርጅትና ከግል ነጋዴዎች መግዛቱንም ኤምባሲው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አስፍሯል።

በአቴናዩም ክለብ ውስጥ ቅርሶቹን ለመቀበል በነበረ ዝግጅት ላይ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እንደተናገሩት እነዚህን ድንቅና ብርቅዬ ቅርሶች በመመለሳቸው ተቋሙን አመስግነዋል።

አምባሳደሩ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶችን የያዙ ሙዚየሞች፣ የቅርስ ሰብሳቢዎችና ግለሰቦች በተመሳሳይ ንብረቶቹን እንዲመልሱ ጥሪ አድርገዋል።

የሻሃራዛድ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታሂር ሻህ በበኩላቸው የቅርሶቹ መመለስ ለኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ስፍራ እንዳለው እንደሚያውቁና ድርጅታቸውንም በመጠቀም በሁለቱ አገራት መካከል ድልድዮችን እንደሚገነቡ ተስፋ አድርገዋል።

ኤምባሲው ቅርሶቹን ወደ ኢትዮጵያ የመመለሱን ተግባር እንደሚያከናውንም ተጠቅሷል።

ከዚህ ቀደምም በጨረታ ሊሸጡ የነበሩና ከመቅደላ የተዘረፉ ሁለት ቅርሶች ሽያጭ እንዲቆም መደረጉ የሚታወስ ነው።

በጨረታ ሊሸጡ የነበሩት ቅርሶች ጥንታዊ መጽሐፍ ቅዱስ ከነ ማኅደሩና መስቀል እንዲሁም ፅዋዎች መሆናቸው በወቅቱ የተገለፀ ሲሆን ጨረታውን ያወጣው የእንግሊዙ በስቢ ኦክሽነርስና ቫሉወርስ የተባለ ድርጅት ነበር።

የጨረታ ድርጅቱና በእንግሊዝ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከድርጅቱ ኃላፊዎች ጋር ያደረገው ውይይትን ተከትሎ ነው ጨረታው እንዲንዲቋረጥ የተደረገው።

የእንግሊዝ ሠራዊት ቅርሶቹን ከመቅደላ ለመውሰድ 15 ዝሆኖችንና 200 በቅሎዎችን ለማጓጓዣነት ተጠቅሞ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

በ2008 ኢትዮጵያ ከመቅደላ የተዘረፉና በሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ ቅርሶቿ እንዲመለሱላት ለተለያዩ የእንግሊዝ ቅርስ ተቋማት ጥያቄ አቅርባ ነበር።

መቅደላ 1868

  • በ19ኛው ክፍለ ዘመን ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ጋር ግንኙነት በመፍጠር አቢሲኒያን ለማዘመን ወሰኑ
  • ነገር ግን የወታደራዊ ድጋፍ ጥያቄያቸው በእንግሊዝ ችላ በመባሉ የአገራቱ ግንኙነት ሻከረ።
  • ለዚህ በምላሹም ቴዎድሮስ የእንግሊዝ ቆንስላና ሌሎች የውጭ አገር ዜጎችን አሰሩ።
  • ይህን ተከትሎ እንግሊዝ ወደ መቅደላው የንጉሡ ቤተ መንግሥት ጦሯን ላከች።
  • በእንግሊዞች እጅ አልወድቅም በማለት አጼ ቴዎድሮስ ራሳቸውን አጠፉ።
  • የእንግሊዝ ጦርም ውድ ብራናዎችን፣ አክሊሎች፣ መስቀል፣ የወርቅ ዋንጫዎችን፣ የንጉሣዊያንና የቤተ ክርስትያን ቁሳቁሶችን ጋሻና የመሳሰሉትን ዘርፈው ወሰዱ።
  • በጊዜው የንጉሡ የሰባት ዓመት ልጅም ወደ እንግሊዝ ተወስዶ በራግቢ ትምህርት ቤት እንዲማር ተደርጓል።
  • ልጃቸው በ18 ዓመቱ በሳንባ በሽታ ሲሞት በዊንድሶር ቤተመንግሥት ተቀበረ።
  • የእንግሊዙ ቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም የወርቅ አክሊልና ዋንጫ አስቀምጧል።
  • ከመቅደላ የተዘረፉት ሌሎቹ ቅርሶች ከግለሰቦች ለሙዚየሙ በስጦታ የተበረከቱ ናቸው።