ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ፈጣሪ ብቻ ነው ከስልጣን ሊያነሳኝ የሚችለው"የብራዚሉ ፕሬዚዳንት
የብራዚሉ ቀኝ ዘመም ፕሬዝዳንት ጃዬር ቦልሶናሮ የአገሪቱ ነጻነት በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር በርካቶችን ያስገረመና አንዳንዶችን ደግሞ ያበሳጨ መልእክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሳኦ ፖሎ ባደረጉት ንግግር '' ፈጣሪ ብቻ ነው ከስልጣን ሊያነሳኝ የሚችለው'' ብለዋል።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ላይ ትችት የሰነዘሩ ሲሆን እነዚህ ተቋማት እሳቸውን እና የፖለቲካ ወዳጆቻቸውን እያጠቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቅርቡ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ላይ ምርምራ እንዲደረግ ፈቃድ መስጡ የሚታወስ ነው።
ፕሬዝደንት ቦልሶናሮ በሚያደርጓቸው በስሜት በተሞሉ ንግግሮች ትችት የሚሰነዝሩባቸውን ሰዎች ከማብጠልጠል ባለፈ የተለያየ አይነት ስም በመስጠትና ሁሌም ተጠቂ እንደሆኑ ለማመላከት ሲጥሩ ይታያሉ።
ደጋፊዎቻቸው ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ይህንን ንግግራቸውን በሚያደርጉባት ሳኦ ፖሎ ከተማ የብራዚልን ባንዲራ በመያዝ ተሰባስበዋል። ድጋፋቸውንና ሁሌም አብረዋቸው እንደሆኑም ሲገልጹ ታይተዋል።
ነገር ግን በቅርቡ የተጀመረባቸው ምርመራ እና እየጨመረ የመጣው ከስልጣን ይውረዱ ጥያቄ ፕሬዝዳንቱ በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጠንከር ያለ እና ቁጣ የተቀላቀለበት መልዕክት እንዲያስተላልፉ አድርጓቸዋል።
ምንም እንኳን ብራዚል ምርጫ የምታካሂደው በመጪው የፈርንጆቹ ዓመት 2022 ጥቅምት ወር ላይ ቢሆንም ከወዲሁ ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ተቀባይነታቸውና ድጋፋቸው እየቀነሰ እንደሆነ እየተገለጸ ነው።
እንዳውም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዝቅተኛ ድጋፍ እንዳላቸው መረጃዎች ጠቁመዋል።
አትላስ ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም በሰራው ጥናት መሰረት 61 በመቶ የሚሆኑት ብራዚላውያን የአገራቸውን መንግስት መጥፎ አልያም እጅግ በጣም ጥፎ ነው ብለው የሚያስቡ ናቸው።
ይህ ቁጥር ደግሞ ፕሬዝዳንቱ በአውሮፓውያኑ 2019 ወደ ስልጣን ሲመጡ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ23 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ፕሬዝዳንቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በአግባቢ መቆጣጠር አልቻሉም በሚል ከስልጣናቸው ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም የታችኛው ኮንግረስ አፈ ጉባኤ ውሳኔውን በመቃወማቸው ቦልሶናሮ በስልጣን እንዲቆዩ ሆኗል።
ይህንን ተከትሎም ፕሬዝዳንቱ ከሁሉም አቅጣጫ ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንደሆነና ኮንግረሱም ሆነ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እሳቸውን ከስልጣን ለማስወገድ እየሰሩ እንደሆነ በተጋጋሚ ይገልጻሉ።
ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንቱ በርካታ ደጋፊዎቻቸውን የሚወክሉ የኢቫንጀሊካል ሃይማኖታዊ መሪዎችን ባገኙበት ወቅት ሶስት ምርጫዎች እንዳላቸው ነግረዋቸው ነበር።
''ወደፊት ሶስት ምርጫዎች ብቻ ናቸው ያሉኝ፤ በቁጥጥር ስር መዋል፣ መገደል ወይም ደግሞ ማሸነፍ'' ብለዋል።
የብራዚል የነጻነት ቀን ላይ ባደረጉተው ንግግርም ይህንኑ አስተያየታቸውን የደገሙ ሲሆን ''ከዚህ በኋላ እኔን ከስልጣን ሊያነሳኝ የሚችለው ፈጣሪ ብቻ ነው'' ሲሉ ተደምጠዋል።
እስከ 140 ሺ የሚደርሱ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎችም በስነስርአቱ በመገኘት የአገራቸውን ባንዲራ እያውለበለቡ ለፕሬዝዳንቱ ያላቸውን ድጋፊ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ቀደም ብለዋ ወደ ዋና ከተማዋ ብራዚሊያ ተጉዘው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸውን አግኝተዋል።
በወቅቱም በርካታ ፖሊሶች በቦታው የነበሩ ሲሆን ደጋፊዎቻቸውም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ነገር ግን ከነበረው የፖሊስ ቁጥር አንጻር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን መቆጣጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በርካታ የቦልሶናሮ ደጋፊዎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ኮንግረስ እንዲዘጉ የጠየቁ ሲሆን ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ፕሬዝዳንቱን እያጠቁ ነው ሲሉም ይከሳሉ።