ለ39 ዓመታት እራሱን ስቶ የቆየው የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አረፈ

ታትሟል

ላለፉት 39 ዓመታት ኮማ ውስጥ የነበረው የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጫዋች ዣን ፒየር አዳምስ በ73 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ሆስፒታል የገባው እአአ ግንቦት 1982 ለጉልበት ቀዶ ሕክምና ነበር። ማደንዘዣ ሲሰጠው በተፈጠረ ስህተት ምክንያት እራሱን ከሳተ በኋላ ለ39 ዓመታት ከኮማ አልነቃም።

ሴኔጋል የተወለደው አጥቂው ዣን ፒየር፤ ለፓሪስ ሴንት ዠርሜን እና ኒይስ ቡድን ከ140 ጊዜ በላይ ተሰልፏል።

ፓሪስ ሴንት ዠርመን (ፒኤስጂ) ባወጣው መግለጫ፤ "ግርማ ሞገስ ያለው፣ ልምድ ያካበተው እና የተከበረው" ሲል ነው ተጫዋቹን የገለጸው።

ኒይስ በበኩሉ ለተጨዋቹ መታሰቢያ መርሃ ግብር እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል።

ዣን ፒየር እአአ ከ1972 እስከ 1976 ፈረንሳይ 22 ዋንጫዎችን እንድታገኝ አስችሏል።

84 ጊዜ ተጫዋቹን ያሰለፈው ኒምስ ቡድን "ለቤተሰቦቹና ለሚወዱት ሰዎች በአጠቃላይ መጽናናት እንመኛለን" ሲል የሐዘን መግለጫ አውጥቷል።

ዣን ፒየር በልምምድ ላይ ሳለ ጉልበቱ ላይ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ነበር ወደ ሆስፒታል የተወሰደው። በእለቱ በሆስፒታሉ የነበሩ አብዛኞቹ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ላይ ነበሩ።

ማደንዘዣ የሚሰጡት ሐኪም ዣን ፒየርን ጨምሮ ለስምንት ህሙማን አገልግሎት እየሰጡ ነበር።

ማደንዘዣ የሚሰጡትን ሐኪም የሚረዳ ተለማማጅ ባለሙያም ሆስፒታሉ ውስጥ ነበር። ተለማማጁ ባለሙያ ኋላ ላይ ለዣን ፒየር ሕክምና የመስጠት አቅም እንዳልነበረው ተናግሯል።

"የተሰጠኝ ኃላፊነት ከአቅሜ በላይ ነበር" ብሏል።

ማደንዘዣ የሚሰጡት ሐኪም እና ተለማማጁ ባለሙያ በሠሩት ስህተት ምክንያት ዣን ፒየር የልብ እና የአዕምሮ ጉዳት ደርሶበታል።

ሁለቱ ባለሙያዎች እስከ 199ዎቹ አጋማሽ ድረስ ለስህተታቸው ሳይቀጡ ቢቆዩም፤ ኋላ ላይ 750 ዩሮ ቅጣት እንዲከፍሉ እና ለአንድ ወር እንዲታገዱ ተወስኗል።

ዣን ፒየር ከ15 ወራት በኋላ ከሆስፒታል ወጥቶ ባለቤቱ በርንዴት በቤታቸው ውስጥ ስትንከባከበው ቆይታለች።

ለአራት አስርት ዓመታት እራሱን ስቶ ቢቆይም፤ ባለቤቱ ግን እስትንፋስ የሚሰጠው መሣሪያ እንዲቋረጥ አልፈቀደችም።

በየቀኑ ልብሱን እየቀየረችለት፣ ምግብ እያዘጋጀችለት፣ ስጦታ እየሰጠችው እና እያዋራችው 39 ዓመታትን አሳልፋለች።

በእርግጥ ዣን ፒየር ኮማ ውስጥ ስለነበረ ለባለቤቱ ምንም ምላሽ አልሰጣትም።

ይረዱት የነበሩ ነርሶች እንደሚሉት ከሆነ፤ በርንዴት ከአጠገቡ ስትለይ እራሱን ስቶ የቆየው ዣን ፒየር አንዳች የስሜት ለውጥ ይታይበት ነበር።

የሕክምና ስህተት የሠራው ሆስፒታል እስከ ዛሬ ድረስ ይቅርታ አለመጠየቁ የዣን ፒየርን ባለቤት ዘወትር ያበሳጫታል።