ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ውስጥ በአስር ሺዎች ደብዛቸው መጥፋቱ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደብዛቸው መጥፋቱ ተገለጸ።
ከ44 ሺህ በላይ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በመላው አፍሪካ እንደጠፉ መረጋገጡን የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (አይሲአርሲ) ዓለም አቀፉን የመጥፋት ቀንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከነዚህም ውስጥ 45 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት ናቸው ብሏል።
ከነዚህ ከጠፉት 82 በመቶ ያህሉ በግጭት ከሚናጡ ከተባሉ ሰባት አገሮች ብቻ መሆናቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
በአፍሪካ ውስጥ ከጠፉት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ከግማሽ በላይ ናይጄሪያውያን ናቸው። በአገሪቱ ውስጥ ወደ 24 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መጥፋታቸው ተመዝግቧል።
በርካቶች የጠፉ ሰዎች ቁጥር የተመዘገበባቸው ሌሎች አገሮች ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ሶማሊያ ፣ ሊቢያ ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ካሜሩን ይገኙበታል።
በኢትዮጵያ ከ3 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ጠፍተዋል በሚል በቀይ መስቀል ተመዝግበዋል።
ከነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ፣ 64 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ደብዛቸው ጠፍቷል የተባሉት በርካታዎቹ ምክንያት ግጭትና ስደት ጋር የተያያዘ እንደሆነም ድርጅቱ አስታውቋል። ከጠፉትም መካከል የ250 የሚሆኑት ጉዳይ በአውሮፓውያኑ 2020 ተከፍቷል።
ድርጅቱ እንዳመለከተው ባለፈው ዓመት በተከሰቱ ግጭቶችና በሌሎች የጥቃት ዓይነቶች አህጉሪቱ የጠፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል።
በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ወረርሽኝ ምክንያት በተጣሉ ገደቦች የጠፉ ተጎጂዎችን ለማግኘት እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማቀላቀል የሚደረገውን ጥረት እያደናቀፉ እንደሆነ ቢገልፅም የጠፉ ሰዎች የተረሱ ሰዎች አይደሉም ብሏል።












