የሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ገዳይ ሲርሃን ሲርሃን እስር ቤት በጩቤ ተወጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የህግ ባለሙያና አሜሪካን በጠቅላይ አቃቤ ህግነት ያገለገሉት ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ገዳይ ተብሎ የእድሜ ልክ እስራት ቅጣት እስር ቤት የሚገኘው ሲርሃን ሲርሃን በካሊፎርኒያ እስር ቤት በጩቤ እንደተወጋ የአሜሪካ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ባለስልጣናቱ እንዳሳወቁት ግለሰቡ የተወጋው አርብ እለት ሲሆን ጥቃቱም እንደደረሰም የእስር ቤቱ ኃላፊዎች በፍጥነት ምላሽ እንደሰጡ ያወጡት መግለጫ አትቷል።
መግለጫው ጥቃት የደረሰበትን ግለሰብ ማንነት ከመግለፅ ቢቆጠብም የአሜሪካ በርካታ ሚዲያዎች ከተለያዩ በፍትህ ዘርፉ ከተሰማሩ ምንጮች እንደተረዱት የ75 አመት እድሜ ባለፀጋው ሲርሃን መሆኑን ነው።
ሲርሃን የእድሜ ልክ እስር ተፈርዶበት ሪቻርድ ዶኖቫን በሚባል ማረሚያ ቤት ነው ያለው። ጥቃት የደረሰበት ማረሚያ ቤቱ ላይ ባለ ታሳሪ ሲሆን ጥቃቱንም ተከትሎ ለብቻው እንዲገለል መደረጉንም የጥቃቱን ዜና በመጀመሪያ ያስነበበው ቲኤምዚ ገልጿል።
ግለሰቡ ለጥቃቱ ምን እንዳነሳሳው ምክንያቱ እየተመረመረ ሲሆን፤ ባለስልጣናቱም ምንም ከማለት ተቆጥበዋል።
ሲርሃን ሲርሃን ማን ናቸው?
ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት እጩነት ቀርበው የነበረውን ሮበርት ኬኔዲ ሎስ አንጀለስ በሚገኘው አምባሳደር ሆቴል በነበሩበት ወቅት ሶስት ጊዜ ሲርሃን ሲርሃን ተኩሶባቸዋል።
ወቅቱ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1968 ሲሆን በሆቴሉ ማዕድ ቤት የተተኮሰባቸው የቀድሞው የሴኔት አባል ፎበርት ኬኔዲ በወቅቱ ካሊፎርኒያ ላይ የነበረውን የዲሞክራቲክ ፓርቲን ድልን ለደጋፊዎቻቸው እያበሰሩ ነበር ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ወንድም ሮበርት ኬኔዲ በተተኮሰባቸው በ24 ሰአታት ውስጥ ህይወታቸው አልፏል።
ቀድሟቸው ከአምስት አመታት በፊት በጎርጎሳውያኑ 1963 ከተገደሉት ወንድማቸው ጆን ኤፍ ኬኔዲም አጠገብ ተቀብረዋል።
ሲርሃን ሲርሃን በመጀመሪያ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን ካሊፎርኒያ የሞት ቅጣትን ስታስቀር ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀየረ።
የዮርዳኖስ ዜግነት ያለው ሲርሃን ትውልዱ ፍልስጥኤማዊ ሲሆን ስለ ተኩሱም ሆነ ስለ ግድያው ምንም ነገር እንደማያውቅ ተናግሮ ነበር።
በጎርጎሳውያኑ 1967 በነበረው የስድስቱ ቀናት ጦርነት ኬኔዲ ለእስራኤል ባደረጉት ድጋፍ እንደከዳን ይሰማኛል በሚል ለአንድ ሚዲያ ተናግሯል ተብሏል።












