የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣትን ኮነኑ

የእንግሊዝ ኃይል

የፎቶው ባለመብት, MOD

ታትሟል

የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣት አሳዛኝና አላስፈላጊ ነው አሉ።

የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት አስተያየት የአሜሪካን ከአፍጋኒስታ መውጣት "አሳዛኝ ፣ አደገኛ እና አላስፈላጊ" ነው ሲሉ ገልፀውታል።

የመስከረም 11 ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ከዩኬ ጋር ወደ አፍጋን ጦሯን ስታስገባ ስልጣን ላይ የነበሩት ብሌየር የአሜሪካን ከሀገሪቱ የመውጣት "ውሳኔ 'የዘላለሙን ጦርነት ማስቀረት' የሚል አላስፈላጊ መፈክርን በመከተል የተወሰነ ነው" ብለዋል።

የጥምር ወታደሮቹ ከሀገሪቱ መውጣት ለጂሃዳውያን ቡድኖች "ፌሽታ" ነውም ሲሉ ተደምጠዋል።

በተጨማሪም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "መውጣት ያለባቸውን ሁሉ እስኪያወጡ" ድረስ ብሪታንያ በአፍጋኒስታን የመቆየት "የሞራል ግዴታ" አለባት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

"ኃላፊነት ያለባቸውን ሰዎች ማስወጣት እና ከለላ መስጠት አለብን - እኛን የረዱን እና ከጎናችን ቆመው የነበሩ በተራቸው ከጎናቸው እንድንቆም የመጠየቅ መብት አላቸው" ብለዋል በድህረ ገጻቸው ባሰፈሩት አስተያየት።

አክለውም ይህ "በቁጭት ሳይሆን ከሰብአዊነት እና ከኃላፊነት በሚመነጭ ጥልቅ ስሜት" መደረግ ይገባዋል ብለዋል።

ከአፍጋኒስታን ለመውጣት የተደረገው ውሳኔ መነሻው ከፖለቲካ የመነጨ ነው ያሉት ብሌየር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተጠቀሙትን "የዘላለሙን ጦርነት" ማቆም የሚል ሐረግ በአስተያየታቸው ጠቅሰዋል።

"ማድረግ አያስፈልገንም ነበር። ግን እሱን መርጠናል"ም ሲሉ አስፍረዋል።

ብሌየር በአፍጋኒስታን ላይ ስህተቶች መፈጸማቸውን ያመኑ ሲሆን ሆኖም "ለስህተቶቻችን የሚሰጡት ምላሾች አለመታደል ሆኖ ተጨማሪ ስህተቶች ነበሩ" የያኔው ውሳኔ " እንከን ያለው" ቢሆንም ፣ "ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የተገኙት መልካም ውጤቶች" አሁን የመቀልበስ ዕድላቸው ሰፊ ነው ብለዋል።

የመውጣቱ ውሳኔ "በዓለም ዙሪያ ያሉ የጂሃዲስት ቡድኖችን በፌሽታ የሚያዘልል" ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

በውሳኔው ሩሲያ ፣ ቻይና እና ኢራን ተጠቃሚ ናቸው ያሉት ብሌየር በምዕራባውያን መሪዎች ቃል የሚገባለት ማንኛውም አካል [ምዕራባውያን መሪዎችን] በጥርጣሬ እንዲመለከታቸው ያደርጋል በማለት አስፍረዋል።

በዚህ ወር መጨረሻ አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ከአፍጋኒስታን ለመውጣት ያስቀመጠችው ቀነ ገደብ ቢሆንም ሰዎችን ለማስወጣት የተወሰ ወታደር ከዚህም ቀን በኋላ ሊቆይ እንደሚችል ፕሬዝዳንት ባይደን አሳውቀዋል።

ጆ ባይደን "ማንኛውም ወደ ሀገሩ መመለስ የሚፈልግ አሜሪካዊ እንዲመለስ እንዳርጋለን" በማለት ቃል የገቡ ሲሆን ፣ ሆኖም የማስወጣቱ ሂደት "በታሪክ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ የአየር በረራዎች" አንዱ እንደሆነ ገልፀዋል።