ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳ ቢያንስ 50 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አገደች
የኡጋንዳ ባለሥልጣናት በአገሪቱ ከሚገኙ አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል ቢያንስ ሃምሳዎቹን ማገዳቸው ተገለጸ።
በድርጅቶቹ ላይ እገዳ የተጣለው ተገቢውን ሕጋዊ ምዝገባ ሳያከናውኑ መንቀሳቀስን ጨምሮ ሌሎች ምክንያቶች ተጠቅሶ ነው።
ከታገዱት በተጨማሪ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሂሳብ መዝገባቸውን ባለማስመርመር እና ዓመታዊ ገቢያቸውን ለሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ባለማቅረባቸው በርካቶች ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ እንደተጣለባቸው ተገልጿል።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚመዘግበውና የሚቆጣጠረው የመንግሥት አካል በኡጋንዳ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኝ ክፍል ነው።
በዚህ ቢሮ እገዳው ከተጣለባቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል አብዛኞቹ በሰብአዊ መብቶችና በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በሐይማኖት ተቋማት የሚደገፉና በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ ናቸው ተብሏል።
ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ ከተጣላባቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል በሰብአዊ መብቶች ጠበቃው ኒኮላስ ኦፒዮ የተመሰረተውና የሚመራው 'ቻፕተር ፎር ኡጋንዳ' የተባለው ይገኝበታል።
ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት እንዳለው ድርጅቱ ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ የሂሳብ መዝገቡን ለምርመራ ሳያቀርብ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል።
ነገር ግን የድርጅቱ መሪ ኦፒዮ መንግሥት ባወጣው የምዝገባ ደንብ መሰረት አስፈላጊውን ሁሉ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በመግለጽ የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገውታል።
አሁን እገዳ የተጣለበት መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት መሪ ኦፒዮ በዚህ ዓመት በሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ተከሰው ታስረው ነበር።
የኡጋንዳ ባለሥልጣናት የግለሰቡ ድርጅት በገንዘብ ምንጭ ዙሪያ ምርመራ አድርገዋል። ግለሰቡ ኋላ ላይ ከእስር በዋስ ቢለቀቁም የቀረበባቸው ክስ ግን አልተዘጋም።
እገዳ ከተጣለባቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ የምርጫ ታዛቢና ምርምር ተቋም ይገኝበታል።
አንድ ሌላ ድርጅት እንዳለው አስፈላጊውን ሕጋዊ መስፈርቶች ቢያሟላም እገዳው እንደተጣለበት አመልክቶ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው ገልጿል።
ድርጊቱንም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መንግሥትን ለሕዝቡ ተጠያቂ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ለማስገደድ ሕገ ወጥ ማድረግና በሕዝብ ፊት የማሳፈር ተግባር ነው በማለት እንዲቆም ጠይቋል።