ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በባንግላዴሽ መብረቅ በሠርግ ላይ የነበሩ 17 ሰዎችን ገደለ
በባንግላዴሽ ውስጥ የሰርግ ስነሰርአት ሲያካሂዱ በነበሩ ሰዎች ላይ በደረሰ የመብረቅ አደጋ ቢያንስ 17 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ሙሽራውን ጨምሮ ሌሎች 14 ሰዎች ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሙሽሪት ግን በስነስርአቱ ቦታ ላይ ስላልነበረች ጉዳት አልደረሰባትም ተብሏል።
ሺግባኒ በምትባለው ከተማ በሚገኝ ወንዝ ላይ በጀልባ የተጓዙት ሰርገኞች ሙሽሪቱን ከቤቷ ለማምጣት ነበር ጉዟቸውን ያደረጉት።
ነገር ግን ልክ የወንዙ ዳርቻ አካባቢ ጀልባቸውን አቁመው በመውረድ ላይ ሳሉ ያልታሰበው መብረቅ ከሰማይ ወርዶ በርካቶችን ገድሏል።
የአካባቢው ነዋሪዎችና አይን እማኞች እንደተናገሩት ሰዎቹ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው መብረቅ ነው የወደቀባቸው።
በደቡባዊ እሲያ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመብረቅ ተመትተው ይሞታሉ።
በአውሮፓውያኑ 2016 ግንቦት ወር ላይ ብቻ ከ200 በላይ ሰዎች በመብረቅ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ባንግላዴሽ መብረቅን ዓመታዊ የተፈጥሮ ስጋት ስትል ፈርጃው ነበር።
በዚሁ ወር በደረሰው የመብረቅ አደጋ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 82 ሰዎች የሞቱበት አጋጣሚ ደግሞ ምን ያክል ስጋት እንደሆነ ትልቅ ማሳያ ነው።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በአገሪቱ የተስፋፋው የደን ጭፍጨፋ ለዚህ አደጋ እንደ ምክንያትነት ሊወሰድ ይችላል። ምክንያቱም ሰዎች መብረቆቹን ሊከላከሉ የሚችሉ በጣም ረጃጅም ዛፎችን ስለሚቆርጡ ነው ይላሉ።