በትግራይ ክልል የኤርትራውያን ስደተኞች ሁኔታ እንዳሳሰበው ተመድ ገለጸ

ታትሟል

በትግራይ ክልል ያሉ ሁሉም ታጣቂ ኃይሎች የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊ ድጋፍ ሕግጋትን መሠረት በማድረግ ለኤርትራውያን ስደተኞች ጥበቃ እንዲያደርጉ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያ ጥሪ አቀረቡ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ልዩ ተጠሪ በትግራይ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ታጣቂ ቡድኖች በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች በተመለከተ በርካታ ተአማኒ ክሶች መቀበላቸውን ተናግረዋል።

በኤርትራ ስላለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ የድርጅቱ ተጠሪ የሆኑት ዶክተር ማሐመድ አብዲልሳላም ባቢኬር እንዳሉት "በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ በኢትዮጵያ ወታደሮች፣ በኤርትራ ሠራዊትና በህወሓት ኃይሎች አማካይነት ስለተፈጸሙ ከፍ ያሉ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊ እርዳታ ሕግጋት ጥሰቶች ተአማኒ ክሶችን" ተቀብለዋል።

"ኤርትራውያን ስደተኞች ተነጥለው በግጭቱ ተሳታፊ ከሆነው ከአንደኛው ወገን ጋር ይተባበራሉ ተብለው በሁሉም ኃይሎች የጥቃት ኢላማ ሆነዋል" ብለዋል።

የተባባሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ዩኤንኤችሲአር እንደሚለው፤ በአሁኑ ወቅት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች መግቢያ አጥተው በተለያዩ ካምፖች ያሉ ሲሆን የረድኤት ድርጅቶችም ድጋፍ ሊያደርጉላቸው አልቻሉም።

በትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ወደ አጎራባች ክልሎች በመዛመቱ በትግራይና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 80 ሺህ ያህል ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ በችግር ላይ ይገኛሉ።

"በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ሚፈጸሙ የበቀል ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ የወሲብ ጥቃት፣ ድብደባና የካምፖች ንብረት ዘረፋን በሚመለከት በሚወጡ ሪፖርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ደንግጫለሁ። ይህ ስደተኞች ላይ የተነጣጠረው ጥቃት መቆም አለበት" ብለዋል ባቢኬር።

በትግራይ ውስጥ ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ወታደራዊ ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት ከጎረቤት አገር ኤርትራ የመጡ 100 ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች በኢትዮጵያ ይገኙ ነበር።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ተቋም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማይ አይኒ እና አዲ ሃሩሽ በሚባሉት የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ 24 ሺህ የሚደርሱ ኤርትራውያን ስደተኞች ሰብዓዊ እርዳታ እንደተቋረጠባቸውና ጥቃቶች እየተፈጸሙባቸው እንደሆነ በመግለጽ ያሉበት ሁኔታ እንሚያሳስበው ገልጾ ነበር።

ባለፈው ጥር ወር ትግራይ ውስጥ ከሚገኙት የስደተኛ መጠለያዎች መካከል ህጻጽና ሽመልባ የሚባሉት ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኙባቸው የነበሩ ካምፖች በመውደማቸው የተነሳ 20 ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች የተፈናቀሉ ሲሆን በርካቶች ደግሞ የት እንደደረሱ አይታወቅም።

"ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች የስደተኞች ካምፖችን ገለልተኝነት እንዲያከብሩ፣ የረድኤት ድርጅቶች በአስቸኳይ የእርዳታ ድጋፍ እንዲያቀርቡ እንዲፈቅዱ እንዲሁም ስደተኞቹ ደኅንነታቸው ወደሚጠበቅባቸው አካባቢ እንዲወሰዱ እንዲያመቻቹ እንጠይቃለን ብለዋል የመንግሥታቱ ድርጅት ተጠሪ።

"ይህ አስፈሪ ሁኔታ መቆም አለበት። ስደተኞችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ከጥቃት መጠበቅ አለባቸው" ሲሉ አሳስበዋል።

ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኙበት በነበረው የአፋር ክልል ውስጥም በቅርቡ ጦርነት በመካሄዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ አስተዳደር አሳውቋል።