ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የሚያስችል የጉምሩክ ታሪፍ ማሻሻያ ይፋ መሆኑ ተገለፀ

ታትሟል

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገውን ጥረት በበለጠ ለመደገፍና ለማሳካት የሚያስችል የጉምሩክ ታሪፍ ማሻሻያ ይፋ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ የግብርናና የአምራች ዘርፉን በመደገፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል የሸቀጦች አመዳደብ ስርዓትን ያለመ ነው የጉምሩክ ታሪፍ ማሻሻያው።

የቀረጥና ታክስ ማሻሻያው እስከ 8 ሺ የሚሆኑ የታሪፍ መስመሮች የሚያካትት ሲሆን ማሻሻያው ትኩረት ያደረገው በጥሬ እቃዎች፣ በከፊል የተመረቱ ግብአቶች፣ ካፒታል እቃዎች እንዲሁም መሰረታዊ የሚባል የፍጆታ እቃዎችን የሚያካትት ነው፡፡

የግብርናና የአምራች ዘርፉን በመደገፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል የቀረጥና የታክስ ማሻሻያው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት እንዲቻል ሁለት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

ይህም የአገር ውስጥ አምራቾች ከታሪፍ አንፃር ከውጭ ከሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች አኳያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው።

የመጀመሪያው አቅጣጫ የምርቱ ዓይነት በአገር ውስጥ በሚፈለገው መጠንና ጥራት የሚመረት ከሆነ ከውጭ በሚገባው ተመሳሳይ ምርት ላይ ከፍተኛ የታሪፍ ምጣኔ ይጣላል።

በዚህም የአገር ውስጥ ምርት ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ ያለመ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ምርቱ በአገር ውስጥ በብቃት የማይመረት ከሆነ በአገር ውስጥ ለሚያመርቱ አምራቾች እነዚህን ምርቶች ለማምረት የሚጠቀሙባቸው በአገር ውስጥ የማይገኙ ግብአቶች በዝቅተኛ የታሪፍ ምጣኔ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ ማድረግ ነው፡፡

በአገር ውስጥ በብቃት የማይመረቱ ምርቶች ላይ ከውጭ በሚገቡበት ወቅት ከፍተኛ የታሪፍ ምጣኔ አይጣልም ተብሏል ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተጠቀሰው የዋጋ ንረት የሚያስከትል በመሆኑ ነው።

ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግ እስከ 8 ሺህ የታሪፍ መስመሮች የሸቀጥ አመዳደብ ስርአትን የያዘ የታሪፍ መለያ ዝርዝር ኮዶችን የያዘ የታሪፍ ጥራዝ (Tariff Book) ተዘጅቷል።

የቀረጥና ታክስ ማሻሻያው በሁሉም ዘርፎች በቀጣይ 10 ዓመታት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትና ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለውም ተብሏል።

ከዚህም በተጫማሪ ማሻሻያው ኢትዮጵያ በንግድ ዘርፍ ለምታደርጋቸው ስምምነቶች መሰረት የሚጥል እንደሆነም ተገልጿል።

ማሻሻያው ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም ከጉምሩክ ኮሚሽን በተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች በተቋቋመ የታሪፍ ኮሚቴ የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።