ታሊባን ወሳኝ ከተማ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የከተማ ላይ ውጊያ እንደተፋፋመ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍጋን መንግሥትና በታሊባን ታጣቂዎች መካከል በወሳኝዋ ከተማ የተቀሰቀሰውና አስፈሪ ነው የተባለው ጦርነት ታሊባን ከአመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውራጃ ከተማን ሊያስለቅቅ ይችላል የሚል ስጋትን ጭሯል።
በደቡባዊ ሄልማን ግዛት ውስጥ በሚገኝ ላሽካር ጋህ በተሰኘ ስፍራ የአሜሪካ እና የአፍጋኒስታን የአየር ላይ ጥቃቶች ቢያደርጉም አከባቢው በታሊባን ታጣቂዎች ከፍተኛ ጥቃት ደርሶበታል።
ታሊባኖች አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተቆጣጥረናል ያሉ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት ከገጠራማ ስፍራዎች የሚሸሹ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሕንፃዎች ውስጥ መጠለላቸው ተነግሯል።
"ዙሪያ ገባውን ውጊያ እየተካሄደ ነው" ሲሉ አንድ ሐኪም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአፍጋኒስታን ጦርን ለማጠናከር በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ሰራዊት ታጣቂዎችን ለመዋጋት የተሰማሩ ቢሆንም አሜሪካ በሀገሪቱ ለ 20 ዓመታት የነበራትን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አቁማ መውጣቷን ተከትሎ ታሊባን በቅርብ ወራት ውስጥ ወደፊት እየገፋ ነው ተብሏል።
የሔልማን ግዛት የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ወታደራዊ ዘመቻዎች ዋና ማዕከል የነበረች ሲሆን ግዛቷ በታሊባን ቁጥጥር ስር የምትገባ ከሆነ ለአፍጋኒስታን መንግስት ከፍተኛ ኪሳራ ስለመሆኑ ተነግሯል።
ታሊባን ላሽካር ጋህን የሚይዝ ከሆነ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2016 በኋላ ታሊባን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚይዘው ዋና ከተማ ይሆናል።
ከተማዋ ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት ከተሰነዘረባቸው ሦስት የክልል ዋና ከተሞች አንዷ ናት።
በከተማዋ ውስጥ የሚገኝ የአፍጋኒስታን ወታደራዊ አዛዥ የታሊባን ድል "በዓለም አቀፍ ደህንነት ላይ አጥፊ ውጤት" ያስከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሜጀር ጄኔራል ሳሚ ሳዳት የተባሉት አዛዡ ለቢቢሲ ሲናገሩ "ይህ የአፍጋኒስታን ጦርነት አይደለም ፣ ይህ በነጻነት እና በፍፁም አምባገነንነት መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው" ብለዋል።
በሄልማን ግዛት ውስጥ 11 ሬዲዮ እና አራት ቴሌቪዥኖች ታሊባን ባደረሳቸው "ጥቃቶች እና ማስፈራሪያዎች" ምክንያት ስርጭታቸውን እንዳቆሙ የአፍጋኒስታን የመረጃ ሚኒስቴር ትላንት [ሰኞ] አስታውቋል።












