የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ

የፎቶው ባለመብት, MANUEL BALCE CENETA

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ሁሉም ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ።

ከአንድ ወር በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል በማስወጣት የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁ የሚታወስ ሲሆን በህወሓት ኃይሎች በኩል ግን ቅድመ ሁኔታዎችን በማቅረብ ተቀባይነት ሳያገኝ ውጊያው ቀጥሏል።

የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ ባቀረቡት ጥሪ ከአስቸኳይ የተኩስ አቁም በተጨማሪ ሁሉን አካታች ፖለቲካዊ ውይይት እንዲደረግና ሁሉም ወገኖች ግጭቱን ከሚያባብሱ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

ኔድ ፕራይስ ጨምረውም በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ያሉት ወገኖች ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ተገቢው መንገድ ወታደራዊ ኃይል ሳይሆን ድርድር መሆን አለበት ብለዋል።

አያይዘውም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ሁሉም ወገኖች ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲያመቻቹ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮምዩኒኬሽን እና የባንክ አገልግሎቶች ትግራይ ውስጥ መልሰው እንዲጀመሩ ጠይቀዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ኔድ ፕራይስ ከአንድ ወር በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን በተመለከተ በትዊታቸው ላይ ያሉት ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከካናዳው አቻቸው ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ያወጀው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት መሆኑን ተናግረው ነበር።

ነገር ግን ህወሓት በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ ጥቃቶችን በመክፈትና የሰብአዊ እርዳታ መተላለፊያ መስመሮችን በመዝጋት ለሰላም የቀረበውን አጋጣሚ አባክኖታል ብለዋል።

በተጨማሪም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር እንዲሁም ለእርዳታ አቅርቦት ሁኔታዎች እንዲመቻቹ የሚያደርገውን ጥረት ከግንዛቤ ባለማስገባቱ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ትግራይ የሚደረግ የእርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ከሰዓታት በፊት በትዊተር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው "የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የአፋርና የአማራ ክልሎች ትግራይ ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው የሚቀርብን እርዳታ በማገድ የሚያገኙት ጥቅም የለም" ሲል ሰብአዊ እርዳታዎች እንዳያልፉ እንዳልተደረገ ገልጿል።

ጨምሮም "የህወሓትን አፍራሽ ተግባር አለማውገዝ የምግብ እርዳታን በመቆጣጠር በሕዝቡ የበላይ ለመሆን የሚያደርገውን ሙከራ ያበረታታዋል" በማለት ቅሬታውን ገልጿል።

የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ጦርነቱ አጎራባች ወደ ሆኑት ክልሎች በመስፋፋቱ የእርዳታ አቅርቦቶች እክል እንዳጋጠማቸው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገልጾ ነበር።

የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው የነበሩት የትግራይ ኃይሎች በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም ለማድረግ የተሻሻለ አዲስ ቅድመ ሁኔታ ሐሙስ ዕለት ይፋ አድርገዋል።

በዚህም ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ለሁሉም አይነት የትራንስፖርት አማራጮች በርካታ መተላለፊያ ኮሪደሮች ክፍት እንዲደረጉ፣ በትግራይ ተቋርጠው የቆዩ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮምዩኒኬሽን፣ የባንክ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና እና የንግድ እንቅስቃሴዎች መልሰው እንዲጀመሩ ጠይቀዋል።