ኒው ዚላንድ የአይ ኤስ አባል የሆነችን ሴት መልሳ ልትቀበል ነው

ታትሟል

እራሱን እስላማዊ መንግስት (አይ ኤስ) እያለ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን አባል በመሆን የተጠረጠረች ሴት ከቱርክ ወደ ኒው ዚላንድ መመለስ ትችላለች ስትል ኒው ዚላንድ አስታወቀች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን የ26 ዓመቷን እናትና እና ሁለት ልጆቿ ወደ ኒው ዚላንድ እንዲመለሱ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ብዙ ንግግሮች መደረጋቸውን አመልክተዋል።

በአውስትራሊያ እና በኒው ዚላንድ ያደገችው ሴት ባለፈው ዓመት የአውስትራሊያ ዜግነቷን እስኪሰረዝ ድረስ የአውስትራሊያ እና የኒው ዚላንድ ጥምር ዜግነት ነበራት።

እአአ በ2014 በአውስትራሊያ ፓስፖርት ወደ ሶሪያ የተጓዘችው ሴት ከሁለት ልጆቿ ጋር ከሶሪያ ወደ ቱርክ ስትገባ ነበር የተያችው። ከተያዘች በኋላ ወደ ኒው ዚላንድ የመጓዝ ፍላጎቷ ፈተና ገጥሞት ነበር።

አውስትራሊያ ባለፈው ዓመት የዚህችን ሴት ዜግነት የቀማች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስኮት ሞሪሰንም "የአገራችን ጠላት" በማለት ጠርተዋት ነበር።

የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚንሰትር ጃሲንዳ አርደርን ሴትየዋ ወደ አውስትራሊያ መመለስ አለባት በማለት ውሳኔውን ተቃውመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ይህች ሴት በሕጋዊነት መኖር የምትችልበት ብቸኛው ቦታ ኒው ዚላንድ ስለሆነች ሴትየዋን ከማስገባት ሌላ ምርጫ እንደሌለ ጠቅላይ ሚንስትሯ ተናግረዋል።

አርደርን "እነሱ የቱርክ ኃላፊነት አይደሉም። አውስትራሊያ ይህን ቤተሰብ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኗ የእኛ ኃላፊነት ያደርጋቸዋል" ብለዋል።

ሴትየዋ ከተመለሰች በኋላ የወንጀል ምርመራ ይደረግባት ወይም አይደረግባት የሚለውን የሚወስነው ፖሊስ ብቻ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚንሰትሯ አክለዋል።

መንግሥታት የሽብር ተጠርጣሪዎችን ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው በሚል ሲወዛገቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

እንግሊዛዊቷ ተማሪ እና እአአ 2015 ላይ አይ ኤስን የተቀላቀለችው ሻሚማ ቤጉምም ጉዳይ በደህንነት ምክንያት የእንግሊዝ ዜግነትዋን የተነጠቀችበት አንዱና ዋነኛው ማሳያ ነው።