ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእስራኤል እና ሞሮኮ መካከል የቀጥታ በረራ ተጀመረ
በሞሮኮ እና በእስራኤል መካከል ተቋርጦ የነበረው የንግድ አውሮፕላኖች የቀጥታ በረራ ትናንት እሁድ በተደረገ ጉዞ እንደገና ተጀመረ።
በሁለቱ አገራት መካከል በረራው እንዲጀመር ያስቻለው ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ላይ ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መስማማታቸው ነው።
ይህ ስምምነት የአረብ አገራት ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ ሲያካሂዷቸው የነበሩ ተከታታይ ስምምነቶች አካል ነው።
ኤል አይ እና አሰረኤይር የተባሉ ሁለት የእስራኤል አየር መንገዶች ከቴል አቪቭ የጎብኚዎች መዳረሻ ወደሆነችው የሞሮኮዋ ማራካሽ ከተማ ተጓዦችን ማመላለስ የጀመሩ ሲሆን አየር መንገዶቹ መደበኛ የጉዞ እቅዶችንም ይፋ አድርገዋል።
የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል አሜሪካ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ይህም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሞሮኮ በምዕራብ ሳህራ ላይ ያላትን የሉአላዊነት ጥያቄ እውቅና ከሰጡ በኋላ ተጠናክሯል።
ሞሮኮ በአንድ ወቅት በሰሜን አፍሪካ ብሎም በመካከለኛው ምስራቅ ካሉ አገራት ከፍተኛ የአይሁድ ማሕበረሰብ መገኛ ነበረች። ወደ ሶስት ሺሕ የሚጠጉ አይሁዶች ብሎም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላዎኢያን ከሞሮኮ ቤተሰቦች የተወለዱ ናቸው።
እስራኤል ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ግፊቶችን እያደረገች ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ሕብረት የታዛቢነት ወንበር ማግኘቷ ይታወሳል።
የቀድሞ ፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር ሱዳን፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ሞሮኮ እና ባህሬን ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዲያወርዱ ያደራደሩ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት የፈረሙት ግብጽ እና ዮርዳኖስ ሲደመሩ፤ ከአረብ ሊግ አባል አገራት ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት የደረሱት አገራት ቁጥር ወደ ስድስት ከፍ አድርጎታል።
ይህ የአረብ አገራት ከእስራኤል ጋር የሚደርሱት የሰላም ስምምነት የፍልስጤም መሪዎች አላስደሰተም። የፍልስጤም መሪዎች እስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ዲፕሊማሲያዊ ግንኙነት እንድትጀምር መፈቀዱ መብታችንን እንድትጋፋ የሚያበረታታ ነው ይላሉ።