አር ኬሊ በአንድ ወንድ ታዳጊ ላይ ጥቃት ፈፅሟል የሚል ክስ ቀረበበት

አርኬሊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አሜሪካዊው የአር ኤንድ ቢ ሙዚቃ ዘርፍ ኮከብ ኤር ኬሊ ከዕድሜ በታች ከሆነ 17 ዓመት ልጅ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸሙን ጨምሮ በአዳዲስ የጥቃት ክሶች ስሙ እየተነሳ ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ እንደሚለው ከሆነ ዘፋኙ በአውሮፓውያኑ 2006 ቺካጎ በሚገኘው የማክዶናልድ ፈጣን ምግብ ሬስቶራንት የተዋወቀውን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በሚገኘው ወጣት ላይ ጥቃት እንዳደረሰበት ገልጿል፡፡

በነሐሴ ወር በአር ኬሊ የፍርድ ሂደት ላይ የዚህን እና ሌሎች የተነሱበት ግን ያልተከሰሰባቸው ጉዳዮች ላይ ማስረጃዎችን ለመስማት ይፈልጋሉ።

አር ኬሊ በማንም ላይ በደል አልፈጸምኩም ሲል የካደ ሲሆን ጠበቆቹም ለአዳዲስ ጉዳዮች ምላሽ አልሰጡም፡፡

የግራሚ-አሸናፊው እና በመዝገብ ስሙ ሮበርት ኬሊ የሚባለው ድምጻዊ በቀጣዩ ወር በህፃናት ወሲባዊ ብዝበዛ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ምስሎችን በማሳየት፣ በማጭበርበር እና ፍትህን በማደናቀፍ በተመሰረተበት ክስ በኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡

ክሶቹ ስማቸው ያልተጠቀሱ ስድስት ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ያካትታል፡፡

ዓቃቤ ህጎች በአር ኬሊ ተበድለናል፣ አስፈራርቶናል ወይም ተጎድተናል የሚሉ ሌሎች ከአስር በላይ ሰዎችን ፍርድ ቤት እንዲሰማላቸው ይፈልጋሉ፡፡

ከእነዚህ መካከል የ 17 ዓመቱን እና ሙዚቀኛ ለመሆን ፍላጎት ያለው ታዳጊ አንዱ ሲሆን ኬሊ በማክዶናልድ አግኝቶት ወደ ቺካጎ ስቱዲዮ ጋብዞት ነበር ተብሏል፡፡

አር ኬሊ ልጁን በሙዚቃ ሥራው ከረዳው በኋላ ዕድሜው ገና ባልደረሰበት ወቅት ወሲባዊ ግንኙነት እንዳደረገ ይነገራል፡፡

ዓቃቤ ሕግ እንደሚለው ልጁ አር ኬሊን በወቅቱ 16 ወይም 17 ዓመት ከሆነው ጓደኛው ጋር እንዳስተዋወቀው እና ከበርካታ ዓመታት በኋላም ከልጁ ጓደኛም ጋር ወሲባዊ ግንኙነት እንደነ፡፡

በተጨማሪም ድምጻዊው በርካታ ሴቶች ከልጁ ጋር ወሲብ እንዲፈጽሙ በማስገደድ ቪዲዮ ይቀርጻቸው ነበርም ብለዋል።

ዓቃቤ ሕግ የሁለቱ ወንዶች ምስክርነት እና የሌሎች ጉዳዮች ኬሊ ከተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊቶችን የሚደግፉ "የተለዩ ክስተቶች ያልነበሩም እናም የአንድ ትልቅ ጉዳይ አካል ነበሩ" ብሏል፡፡

ዳኛው ማስረጃዎቹ ከግምት ውስጥ ይገባሉ በሚለው ላይ ገና ውሳኔ አልሰጡም፡፡

ከ 1990 ዎቹ ታላላቅ የአር ኤንድ ቢ ኮከቦች አንዱ የነበረው ኬሊ ለሁለት ዓመታት ያህል በእስር ቆይቶ ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

የኒው ዮርክ ችሎቱ ነሐሴ 9 ቀን እንዲጀመር ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡