ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያ 450,000 በላይ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቶች ከአሜሪካ ተበረከተላት

ታትሟል

የአሜሪካ መንግሥት ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባቶችን ለኢትዮጵያ ለገሰ።

መጠናቸው 450 ሺህ በላይ የሆኑ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቶች ዛሬ ሐምሌ 12/ 2013 ዓ. ም. አዲስ አበባ መድረሳቸው ተጠቁሟል።

ክትባቱ በተበረከተበት ጊዜ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጌታ ፓሲ እንዳሉት፤ ክትባቱ ኢትዮጵያውያንን ከኮሮናቫይረስ ለመታደግ በማገዝ ወረርሽኙ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ያሳደረውን ጫና ይቀንሳል ተብሎ ይታመናል።

ኢትዮጵያ ከወራት በፊት የወረርሽኙን መከላከያ ክትባት መስጠት የጀመረች ሲሆን፤ የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ክትባት በጤና ተቋማት መሰጠት ጀምሯል።

400 ሺህ የአስትራዜኒካ ክትባት ለሁሉም ክልሎች እየተሰራጨ እንደሚገኝና በቀጣይም 1.7 ሚሊዮን ክትባት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ሚንስትሯ ተናግረዋል።

የትራንስፖርት ዘርፍ ሠራተኞች፣ ፖሊሶች፣ መምህራን፣ የባንክና የፍርድ ቤት ሠራተኞች፣ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው እና በእድሜ የገፉ ዜጎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።

453,600 የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት አዲስ አበባ መድረሱን በማስመልከት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ እንደገለጸው፤ የአሜሪካ መንግሥት ክትባቶቹን በመለገስ ሂደት ውስጥ ከአፍሪካ ሕብረት እና የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር ተቋም (ሲዲሲ) ጋር በቅርበት ሠርቷል።

ኤምባሲው "ክትባቶቹ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ከወረርሽኙ ለመከላከል ያግዛሉ። የሁለትዮሽ ግንኙነታችንንም ያጠናክራል" ሲል በማኅበራዊ ገጹ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት-ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ቅርንጫፉ በኩል እንዳስታወቀው፤ ክትባቶቹ ኢትዮጵያ እንዲደርሱ ዩኒሴፍ ድጋፍ አድርጓል።

ይህም ኮቫክስ በተባለው ዓለም አቀፍ የክትባት ስርጭት አስተባባሪ አማካይነት ነው። ኮቫክስ የኮሮናቫይረስ ክትባት በፍትሐዊነት እንዲከፋፈል የሚሠራ ዓለም አቀፍ ጥምረት ነው።

ለኢትዮጵያ የተለገሰው ክትባት፤ አሜሪካ ለአፍሪካ ለመስጠት ቃል የገባቸው 25 ሚሊዮን የኮሮናቫይረስ ክትባት ውስጥ ይካተታል።

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 2,134,954 ዜጎቿን የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባትን እንደከተበች የጤና ሚንስትር ገልጿል።

የአሜሪካ መንግሥት በኮቫክስ በኩል 12 ሚሊዮን ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ለተለያዩ ታዳጊ አገራት እንደሚለግስ ማስታወቁ ይታወሳል።

የመጀመሪያው ዙር ልገሳ የተደገው ለአፍጋኒስታን ሲሆን፤ 1.5 ሚሊዮን ክትባቶች ከሳምንት በፊት ወደ አገሪቱ መላካቸው ተገልጿል።

ለብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ሜክሲኮ እና ደቡብ ኮርያ ክትባቶች መከፋፈላቸውም ተመልክቷል።

በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ድረ ገጽ ላይ እንደተጠቀሰው፤ ድርጅቱ ለኮቫክስ ጥምረት ክትባቶችን የሚለግሰው የአሜሪካ መንግሥት፣ ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን እና ጋቪ ጋር ባደረገው የሦስትዮሽ ስምምነት ነው።

የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ዋና የሳይንስ ኃላፊና የዋና ኮሚቴው ምክትል ሊቀ መንበር ዶ/ር ፖል ስቶፍልስ "ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ክትባቱ በዓለም በእኩል ደረጃ እንዲከፋፈል ማስቻልን ያማከለ ነው" ብለዋል።

ድርጅቱ እአአ 2022 ድረስ 900 ሚሊዮን የክትባት ጠብታዎችን በቀጥታ ለኮቫክስ እና የአፍሪካ ሕብረት ለመለገስ ቃል መግባቱን በድረ ገጹ አስታውቋል።

ሀብታም አገራት የክትባት ክምችታቸውን ለደሃ አገራት እንዲለግሱ በተደጋጋሚ ጥሪ ተደርጓል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በተደጋጋሚ የክትባቱ ክፍፍል ፍትሐዊ እንዲሆን ማሳሰባቸው አይዘነጋም።