የ18 ዓመቱ ወጣት ከቀናት በኋላ ከጄፍ ቤዞስ ጋር ወደ ጠፈር ሊበር ነው

የፎቶው ባለመብት, BLUE ORIGIN
የ18 ዓመት ወጣት የሆነው ኦሊቨር ዳኤሜን የፊታችን ማክሰኞ ሐምሌ 13 ጄፍ ቤዞስ ወደ ጠፈር በሚያደርገው በረራ ተሳታፊ እንደሚሆነ ተገለጸ።
ይህም ወደ ጠፈር የበረረ በእድሜ አነስተኛ ሰው ያደርገዋል። ወጣቱ ይህን እድል ያገኘው ወደ ጠፈር ለመብረር በ28 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ ያሸነፈ ግለሰብ መብረር ሳይችል በመቅረቱ ነው ተብሏል።
ማንነቱ ያልተገለጸው ግለሰብ በዕለቱ ወደ ጠፈር መሄድ ያልቻለው ሌላ ጉዳይ ስለገጠመው ነው ብሏል የጄፍ ቤዞስ ብሉ ኦሪጅን ኩባንያ።
ኦሊቨር ዳኤሜን፤ ሶመርሴት ካፒታል ፓርትነርስ የተባለ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ጆስ ዳኤሜን ልጅ ነው።
ዋና ሥራ አስኪያጁ በሁለተኛ ዙር ወደ ጠፈር ለሚደረገው በረራ ቲኬት ቆርጠው የነበረ ሲሆን በስም ያልተገለጸው ግለሰብ መብረር ሳይችል መቅረቱን ተከትሎ ዋና ሥራ አስኪያጁ የእርሱን ቦታ እንዲወስዱ ሲጠየቁ በእርሳቸው ፈንታ ልጃቸው እንዲበር ማድረጋቸውን ብሉ ኦሪጅን ገልጿል።
ወጣቱ በረራውን የሚያደርገው ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር ነው። የ82 ዓመቱ ዊሊ ፈንክ፣ ጄፍ ቤዞስ እና የጄፍ ቤዞስ ወንድም ማርክ የፊታችን ማክሰኞ ወደ ጠፈር ይበራሉ።
የፊዚክስ ተማሪ እንደሆነ የተገለጸው የ18 ዓመቱ ወጣት፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ለጠፈር፣ ጨረቃ እና ሮኬቶች ሳይንስ ከፍተኛ ፍቅር ነበረው ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኩባንያው ተጓዦቹን ከመሬት ወደ ጠፈር 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ይዞ ለመሄድ ያሰበ ሲሆን፤ ይህም ተጓዦች የመሬት ስበት የሌለበትን ሁኔታ የማግኘት ልምድ ይኖራቸዋል ተብሏል።
ጄፍ ቤዞስ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለ ጸጋ ሰው ሲሆን እአአ 2000 ላይ የመሠረተው ብሉ ኦሪጅን ኩባንያ እርሱ እና ወንድሙ ወደ ጠፈር እንደሚበሩ ከአንድ ወር በፊት ይፋ አድርጎ ነበር።
ጄፍ ቤዞስ ወደ ጠፈር መብረር በሕይወቱ ማሳካት የሚፈልገው ትልቁ ነገር እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገልጻል።
ይህ የጠፈር ጉዞ የሚከናወነው ከአንድ ሳምንት በፊት እንግሊዛዊው ሰር ሪቻርድ ብራንሰን ቨርጅን ጋላክቲክ በተሰኘ ሮኬት አውሮፕላናቸው ወደ ጠፈር በረራ አድርገው ከተመለሱ በኋላ ነው።












