ጣሊያን ስፔንን በመርታት ለፍጻሜ መድረሷን አረጋገጠች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአውሮፓ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ጣልያን ስፔንን በፍጹም ቅጣት ምት በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረሷን አረጋገጠች።
በእንግሊዙ ዌምብሌይ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዘጠና ደቂቃው እና ተጨማሪ ደቂቃ አንድ አቻ በመጠናቀቁ ሁለቱ ቡድኖች በፍጽም ቅጣት ምት እንዲለያዩ ሆኗል።
የስፔኑ የፊት መስመር ተጫዋች አልቫሮ ሞራታ የስፔንን የመጨረሻውን ፍጹም ቅጣት ምት የሳተ ሲሆን የጣልያኑ ጆርጂንዮ ደግሞ ፍጹም ቅጣት ምቱን ወደ ግብ መቀየሩን ተከትሎ ጣልያን ዛሬ ምሽት ከእንግሊዝና ዴንማርክ አሸናፊ ጋር ለፍጻሜ በመጪው እሁድ ትጫወታለች።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በፈጣን እንቅስቃሴና በስፔን የተበላይነት የተሞላ ቢሆንም ግብ ግን ሳይቆጠር ነበር የተጠናቀቀው። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የጣልያኑ ፌደሪኮ ኪዬዛ አስገራሚ ግብ አስቆጥሮ ጣልያንን መሪ ማድረግ ችሏል።
ነገር ግን ጨዋታው ሊጠናቀቅ እየተቃረበ በነረበት ሰአት የስፔን ተጫዋቾች በጥሩ ጨዋታ ጣልያን የግብ ክልል ውስጥ የተቀባበሏትን ኳስ ተቀይሮ የገባው አልቫሮ ሞራታ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር አገሩን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር።
የጣልያኑ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ ያዋቀሩት ቡድን እስካሁን ድረስ ብዙም ሳይቸገር ነበር ለግማሽ ፍጻሜው መድረስ የቻለው። ነገር ግን ከስፔን ጋር የተደረገው ጨዋታ ጣልያኖችን የፈተነ ነበር። የስፔኑ አሰልጣኝ ሊዊስ ኤነሪኬ የጣልያንን አጨዋወት በሚገባ አጥንተውና ኳስን መሰረት ያደረገ ጨዋታ ላይ አተኩረው ነበር የጀመሩት።
በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ እንደ ሞራታ ብዙ ግብ የሚሆኑ እድሎችን ያባከነ የለም በሚል በርካቶች ሲወቅሱት የነበረ ሲሆን ስፔን ውስጥም ቤተሰቦቹ ዛቻ ደርሶባቸዋል። ነገር ግን በግማሽ ፍጻሜው አገሩን አቻ አድርጎ ነገሮችን መለወጥ ቢችልም ፍጹም ቅጣት ምቱን መሳቱ ደግሞ ተመልሶ ጫና ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
ጣልያን ከምድብ ድልድል ጀምሮ ባልተለመደ መልኩ ማጥቃት ላይ መሰረት ያደረገና ብዙ ግቦችን ማስቆጠር የሚያስችል አጨዋወት ነበር ይዛ የመጣችው። ነገር ግን ከስፔን በነበረው ጨዋታ ወደቀድሞው መከላከልን ማዕከል ያደረገ አጨዋወት ተመልሰው ነበር።
አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ ብሄራዊ ብድኑን ከተረከቡ ወዲህ ለ2018ቱ የዓለም ዋንጫ እንኳን ጣልያንን ማሳለፍ አቅቷቸው የነበረ ቢሆንም በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ግን በደንብ የተደራጀና ውጤታማ ቡድን ሰርተው ለፍጻሜ መድረስ ችለዋል።
ዛሬ ምሽት አራት ሰአት ላይ ደግሞ ሌላኞቹ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች ዴንማርክና እንግሊዝ ይገናኛሉ። የዚህ ጨዋታ አሸናፊ የፊታችን እሁድ በሚካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ከጣልያን ጋር ይፋለማል።












