ቫቲካን ጳጳሷን ገንዘብ በማጭበርበር ፍርድ ቤት ልታቆማቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቫቲካን የሮማው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ ቀኝ እጅ የሆኑትን ካርዲናል (ሊቀ ጳጳስን) ጨምሮ አስር ግለሰቦች ከገንዘብ ማጭበርበር ጋር በተገናኘ የፍርድ ሂደት እንዲጀመር አዛለች።
በዚህ የተካተቱት ሊቀ ጳጳስ አንጄሎ ቤኩ በቫቲካን ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው ሲሆን በገንዘብ ማጭበርበርና ስልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምም እንደሚከሰሱ ተጠቁሟል።
የ73 አመቱ ጳጳስ ምንም ስህተት አልፈፀምኩም ብለው የሚከራከሩ ሲሆን ከስልጣናቸው በመስከረም ወር ለቀዋል ነገር ግን ማዕረጋቸው እንዳለ ነው።
ክሶቹ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የቤተ ክርስቲያኗን ገንዘብ በማውጣት በለንደን የንብረት ግዢ ጋር የተያያዙ ናቸው።
ካርዲናል አንጄሎ የፖፕ ፍራንሲስ የቅርብ አማካሪ የነበሩ ሲሆን ከዚህ ቀደምም የቤተ ክርስቲያኗን መዋጮ በሚያስተዳድረው የቫቲካን የመንግሥት ፅህፈት ቤት ቁልፍ ስራ ነበራቸው።
በፅህፈት ቤቱ ውስጥ በኃላፊነት ላይ እያሉ በለንደን ቅንጡ ህንፃ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ አወዛጋቢ ኪሳራ ስምምነት ስለተዳረገውም ውል ጥያቄ ይቀርብባቸዋል። ስምምነቱ የገንዘብ ምርመራ እየተደረገበት ነው።
በስሎአን ጎዳና ለሚገኘው አፓርትመንት የተከፈለው 200 ሚሊዮን ዶላር ከሌላ አገራት ካሉና ከኩባንያዎች በመጣ ገንዘብ ነው በሚል ካርዲናሉ ውሉን ደግፈው እየተከራከሩም ነበር።
ካርዲናሉ ለእሳቸው ቅርብ በሆኑ ሰዎች አማካኝነት ባወጡት መግለጫ "የሴራ ሰለባ ነኝ" በሚል የቃወሙት ሲሆን "ፍፁም ንፁህ ነኝ" ማለታቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።
በቫቲካን ውስጥ ያለውን ውስብስብ የገንዘብ ሁኔታ መቋጫ ማግኘትም የፖፕ ፍራንሲስ ዋነኛ ስራ ሆኗል። ፖፑ ከዚህ በተጨማሪም የሰው ልጅ ፍፁም ባይሆንም ጉድለቶች ቢኖሩበትም ቤተ ክርስቲያኗ የሁሉም ናት የሚል እምነትን ይዘው እየሰሩ ይገኛሉ።
ቤተ ክርስቲያኗ ራሳቸውን በመንፈስ ለማበልፀግ የሚፈልጉ ሁሉ ክፍት ናት የሚልም መልዕክት በማስተላለፍ ይታወቃሉ።
ካርዲናሉ የቀረበባቸው ወንጀል በፍርድ ቤት ቀርቦ መረጋገጥ አለበት።












