ለአውሮፓ ሻምፒዮንነት ቀሪዎቹ ስምንት አገራት ፍልሚያቸውን ዛሬ ይጀምራሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊነት የሚፎካከሩት ቀሪዎቹ ስምንት አገራት ፍልሚያቸውን ዛሬ ምሽት ይጀምራሉ።
የዩሮ 2020 የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ስዊዘርላንድ ከስፔን በሚያደርጉት ጨዋታ ነው የሚጀመሩት።
ስዊዘርላንድ ትልቅ ግምት የተሰጣትን ፈረንሳይን በጥሎ ማለፍ ጨዋታ በፍጹም ቅጣት ምት በማሸነፍ ነው ለሩብ ፍጻሜው የደረሰችው።
ስፔን በበኩሏ ክሮሺያን 5 ለ 3 በማሰነፍ ነው ለዛሬው ጨዋታ የበቃችው።
ስዊዘርላንድ እና ስፔን በጥሎ ማለፉ ጨዋታ ተጨማሪ ሰዓት ድረስ ለመጫወት የተገደዱ ቡድኖች ናቸው። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሴንት ፒተርስበርግ ሩሲያ ላይ ይካሄዳል።
የምሽቱ ሁለተኛ ጨዋታ ለዋንጫው ትቅል ግምት ያገኙትን ሁለት ቡድኖች ያገናኛል - ቤልጅየም ከጣሊያን።
ቤልጂየም በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ፖርቹጋልን 1ለ 0 በማሸነፍ ነው ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለችው።
ለንደን ላይ በተደረገ ግጥሚያ ጣሊያን እስከ ተጨማሪ ሰዓት በዘለቀ ጨዋታ ኦስትሪያን 2 ለ 1 አሸንፋለች። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጀርመን ሙኒክ ይካሄዳል።
የዛሬ ምሽት ጨዋታ አሸናፊዎች ለፍጻሜ ለማለፍ ማክሰኞ ምሽት ለንደን ላይ ግጥሚያቸውን ያደርጋሉ።
ሌሎች የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ነገ ምሽት ይደረጋሉ።
የመጀመሪያው የአዘርባጃን ባኩ ጨዋታ ቼክ ሪፐብሊክ እና ዴንማርክን ያገናኛል።
ቼክ ሪፐብሊክ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ኔዘርላንድስን 2 ለ 0 በማሸነፍ ነው ለነገው ጨዋታ የደረሰችው። ዴንማርክ በበኩሏ አምስተርዳም ላይ ዌልስን 4 ለ 0 ማሸነፍ ችላለች።
በነገው ሁለተኛው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ዩክሬን እና እንግሊዝ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ዩክሬን በጥሎ ማለፉ ጨዋታ ስዊዲንን ግላስጎው ላይ 2 ለ 1 መርታት ችላለች።
እንግሊዝ በበኩሏ ለንደን ላይ ባደረገችው ጨዋታ ጀርመንን 2 ለ 0 በማሸነፍ ነው ለነገው ጨዋታ የደረሰችው።
ዩክሬን ከእንግሊዝ የሚያደርጉ ጨዋታ ጣሊያን ሮም ላይ የሚካሄድ ይሆናል።
ነገ በሩብ ፍጻሜው የሚጫወቱት ቡድኖች አሸናፊዎች ለዋንጫ ለማለፍ ለንደን ላይ ይጫወታሉ። የዩሮ 2020 ፍጻሜ ጨዋታ በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ ለንደን ዌምብሌይ ላይ በሚደረግ ጨዋታ ይጠናቀቃል።












