ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን 'በቀናት ውስጥ' ጠቅልሎ እንደሚወጣ ተገለፀt
የአሜሪካ ጦር በቀናት ውስጥ ከአፍጋኒስታን ጠቅልሎ እንደሚወጣ አንድ ሪፖርት አመላክቷል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ለሮይተርስ እንደተናገሩት የአሜሪካ ኤምባሲና የካቡል አየር ማረፊያን የሚጠብቁ ኃይሎች ይቀራሉ ብለዋል።
ነገር ግን በቅርቡ አንድ የአሜሪካ የጦር ኮማንደር የአሜሪካ ጦር ጠቅልሎ የሚወጣ ከሆነ አገሪቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገባለች በማለት ከሰሞኑ አስጠንቅቀዋል።
በባለፈው ወር የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣቱን ተከትሎ ውጊያው በከፍተኛ ሁኔታ እንደተቀጣጠለ ተገልጿል።
በቅርቡም ታሊባን በርካታ ግዛቶችን በመቆጣጠር ድል ቀንቶታል ተብሏል።
ሲኤንኤን በበኩሉ ሮይተርስ ያገኘውን ሪፖርት ከአሜሪካ ባለስልጣናት ማረጋገጥ ችሏል።
"ይህ ሳምንት ጠቅልሎ ለሚወጣው የአሜሪካ ጦር ወሳኝ ወቅት ነው" በማለት ስማቸው ያልተጠቀሰ የመከላከያ ባለስልጣን ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
650 የሚሆኑት ወታደሮች በአፍጋኒስታን እንደሚቆዩና በካቡል የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ይጠብቃሉ ተብሏል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎችም እንዲሁም የከተማዋን አየር ማረፍያ ለመጠበቅ እንደሚሰማሩ ተገልጿል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጦሩ ጠቅልሎ መውጣት አለበት ያሉት ቀነ ገደብ መስከረም አንድ ነበር። ነገር ግን በቅርብ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በቅርብ ወራት እንዲሰማሩ የተደረጉት ከ4 ሺህ በላይ ወታደሮች ከተቀመጠው ቀን በፊት እስከ ሃምሌ አጋማሽ እንደሚወጡም ተጠቁሟል።
አወጣጣቸውም ፈጥኗል ተብሏል።
ማክሰኞ እለት ጄኔራል ስኮት ሚለር እንደተናገሩት የአፍጋኒስታን መሪዎች መተባበር ካልቻሉ አለም አቀፍ ወታደሮች ሲወጡ ለአገሪቷ"ክፉኛ ፈታኝ ጊዜ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።
በአፍጋኒስታን ያለውን የአሜሪካ ዘመቻ የጦር ኮማንደር ማስጠንቀቂያ በተጨማሪ የታሊባን በርካታ ግዛቶችን መቆጣጠሩ አስከፉ ሁኔታዎችን ይፈጥራል በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል።
ታጣቂዎች ከግንቦት ጀምሮ ከ370 ግዛቶች 50ዎቹን ተቆጣጥረዋል ተብሏል። መዲናዋን ካቡልን ጨምሮ በርካታ ከተሞችንም መክበባቸው ተነግሯል።