የአየር ንብረት፡ በካናዳ በተከሰተ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ሙቀት በርካቶች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በካናዳ ባልተጠበቀና እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛ ነው በተባለ ሙቀት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።
የካናዳ ምዕራባዊ ግዛት በሆነችው ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ፖሊስ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ 70 ለሚጠጉ ድንገተኛ ሞቶች ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል።
ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ አረጋውያን ናቸው ብሏል።
ፖሊስ እንዳለው በአካባቢው ያጋጠመው ከፍተኛ ሙቀት ለሕልፈታቸው ምክንያት ነው።
ማክሰኞ ዕለት በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው ሊይተን ለሦስት ተከታታይ ቀናት በታሪኳ ከፍተኛ የተባለውን የሙቀት መጠን መዝግባለች። ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው የሙቀት መጠን -49.5 ዲግሪ ሴልሽየስ ወይም 121 ዲግሪ ፋራናይት ነው።
ከዚህ ሳምንት በፊት በካናዳ ያለው የሙቀት መጠን ከ45 ዲግሪ ሴልሽየስ አልፎ አያውቅም ነበር።
ተቀማጭነቱን ቫንኩቨር ያደረገው ካናዳዊው የፖሊስ አዛዥ ማይክ ካላንጂ "ጎረቤቶቻችሁን፣ የቤተሰብ አባላቶቻችሁን፣ እንዲሁም ታላላቆቻችሁን ደህና መሆናቸውን ጠይቁ" ሲሉ መክረዋል።
የፖሊስ አዛዡ አክለውም "የአየር ጠባዩ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም አረጋውያንንና የጤና እክል ያለባችውን ሰዎች ሊገድል ይችላል፤ በመሆኑም ደህና መሆናቸውን መጠየቅ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
እንደ ፖሊስ ከሆነ በበርናቢይ እና ሰሪይ በምትገኘው በቫንኩቨር የባህር ዳርቻ ከተማ ሙቀቱ ለ69 ሰዎች ሞት መንስዔ እንደሆነ ይታመናል።
አብዛኞቹ አረጋውያንና እና አሳሳቢ የጤና ችግር ያላባቸው ናቸው።
በትንሿ የካናዳ መንደር ሊይተን ነዋሪ የሆኑት ሜጋን ፋንድሪክ "ከቤት መውጣት የማይታሰብ ነበር" ሲሉ ግሎብ ኤንድ ሜይል ጋዜጣ ተናግረዋል።
"ሙቀቱ ከአቅም በላይና የማይቻል ነው" የሚሉት ነዋሪዋ፤ በአንጻራዊነት ሙቀቱ ወደሚቀንስበት የብሪቲሽ ኮሎምቢያ አካባቢ ልጄን ልኬያለሁ ብለዋል።
የአየር ሁኔታ ትንበያን የሚገልጸው ኢንቫይሮመንት ካናዳ፤ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ እና አልበርታ ከፍተኛ ሙቀት ሊከሰት እንደሚችል ቀደም ሲል አስጠንቅቆ ነበር።
በኢንቫይሮመንት ካናዳ የአየር ንብረት ባለሙያ የሆኑት ዴቪድ ፊሊፕ "በዓለማችን ሁለተኛው ቀዝቃዛና በረዷማ አገር ነን፤ ቅዝቃዜና በረዶ እንጅ እንደዚህ ስለሙቀት ብዙ ጊዜ አናወራም፤ አሁን ላይ ግን እዚህ ከምናየው አንጻር ዱባይ ቀዝቃዛ ልትሆን ትችላለች" ብለዋል።












